ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ የተሻለ ቁጥጥርና የክትትል ለማድረግ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች፣ መመሪያዎች እና ደንቦችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገለጸ

ድሬዳዋ ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ የተሻለ ቁጥጥርና የክትትል ለማድረግ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች፣ መመሪያዎች እና ደንቦችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገለጸ።

ኅብረተሰቡም ህገ ወጥ የመድኃኒት እና የምግብ ቁጥጥር ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ለሶስት ቀናት በድሬዳዋ ያካሄደው የባለፈው በጀት ዓመት ግምገማና የተያዘው በጀት ዓመቱ እቅድ ላይ ያተኮረው ውይይት አጠናቋል።

በጉባዔው ክልሎች፣ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በመድኃኒት ቁጥጥር እና ክትትል ዘርፎች ያከናወኗቸውን ስራዎች በመገምገም በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አቅጣጫዎች ተቀምጧል።

በተጨማሪም ባለስልጣኑ፣ ክልሎችና ሁለቱ  የከተማ አስተዳደሮች በጋራ የሚያከናውኗቸው ዕቅዶች በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ ለመተግበር የሚያስችላቸው መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣንዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ እንደተናገሩት ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ ቁጥጥርና የክትትል ለማድረግ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች፣ መመሪያዎች እና ደንቦችን ተግባራዊ ያደርጋል።

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችም ጥራት ያላቸው፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን በብዛትና በጥራት እንዲያመርቱ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ፈጣንና ዘመኑን የሚመጥን የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች በማጠናከር በዘርፉ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡ የምግብና የመድኃኒት ውጤቶች ላይ የሚካሂደው ቁጥጥርና ክትትል በማጠናከር በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶችን ለመቆጣጠር ከፍትህና ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ በተለይ በቁጥጥር ስራ ውስጥ ጥቆማ በመስጠት እና ከፀጥታ አካላት ተቀናጅቶ ችግሩን በመከላከል እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ እንዲያጠናክር ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።

ህገ ወጥ የምግብና መድኃኒት  ዝውውር  ከአገር ደህንነትና ፀጥታ ጋር የሚገናኝ  ጭምር በመሆኑ የቁጥጥር ሥርዓቱ ይበልጥ  ይጠናከራል ብለዋል።

የስራ መግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሁሉም ክልሎች የዘርፉ አመራር አባላት በበጀት ዓመቱ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ በመስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም