ቀጥታ፡

የ"ሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ "መረጃ  በመመዝገብ  ለአገር ልማታዊ ዕቅድ ስኬት ሁሉም የድርሻውን  መወጣት እንዳለበት  ተገለጸ

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 25/2016 (ኢዜአ) ፡- የ"ሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ "መረጃ  መዝግቦ በመያዝ ለአገር ልማታዊ ዕቅድ ስኬት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ። 

7ኛው የ"ሲቪል ምዝገባ እና  ቫይታል ስታቲስቲክስ " ቀን በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው። 

በበዓሉ ላይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ  ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት፤ የ"ሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ "መረጃ ለአንድ አገር እድገትና ለዜጎች መብት መከበር ያለው ፋይዳ የላቀ ነው።

የዘላቂ ልማት ግቦች ዕቅድ ለማሳካት የ"ሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ "መረጃ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውም ሰው በህግ ፊት የመታወቅ መብት አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤  ሁሉም ሰው የልደት ምዝገባን ጨምሮ ህጋዊ የማንነት ማረጋገጫ ማስረጃ ሊኖረው እንደሚገባ  ገልጸዋል።

ይህም  ሁሉም ዜጋ የልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ ምዝገባዎችን በአግባቡ ማድረግ እንዳለበትና ለዚህም ተገቢውን ማስረጃ ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግብ በተቀመጠው መሰረት በ2030 ዓ.ም የልደት ምዝገባ መቶ  በመቶ እንዲሁም የሞት ምዝገባን 80 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል። 

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ለኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ሁሉ መረጃ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።


 

ለሁሉም ዕቅዶች መነሻ መረጃ በመሆኑ በክልሉ መረጃ ለግለሰብ፣ ለህዝብና ለአገር ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር በየደረጃው ያሉ አመራር አባላት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሆኖም  በአንዳንድ አካባቢ የአመራሩና የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ምክንያት ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ፤ የ"ሲቪል ምዝገባና ቫይታል ስታቲስቲክስ"  መረጃ የሚካሄደውን የልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማሳካት ትልቁ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም የ"ቫይታል ስታቲስቲክስ" መረጃ በአግባቡ ለመያዝ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ቢሆኑም  የምዝገባው ሽፋን ምጣኔ ከሚጠበቀው አንጻር አነስተኛ  መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ፣ የልማት ችግር፣ የአደረጃጀት ጉድለትና የአመራር ትኩረት አለመስጠት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማስተካከል ሁሉም በየደረጃው ያለ አመራር በማስተባበርና በመምራት እንዲሁም ግንዛቤ በመስጠት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበዓሉ ላይ  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም