የጤና ዘርፍ ተመራቂዎች በክልሉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ማገዝ አለባቸው -- አቶ አንተነህ ፍቃዱ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ዘርፍ ተመራቂዎች በክልሉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ማገዝ አለባቸው -- አቶ አንተነህ ፍቃዱ
ሆሳዕና፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦የጤና ዘርፍ ተመራቂዎች በክልሉ የጤና አገልግሎትን በጥራትና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት እንዲያግዙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ አሳሰቡ።
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ27ኛ ዙር በመጀመሪያ ዲግሪና በዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን 561 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል 141ዱ በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ ሲሆን፣ በዲፕሎማ የተሰጠውን ሥልጠና የተከታተሉት ደግሞ 420 ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳስገነዘቡት ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታ የቀሰሙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ጤና መጠበቅ ማዋል ይጠበቅባቸዋል።
"የዛሬ ተመራቂዎች ለክልሉ ማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ መሻሻል የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት የጤና አገልግሎትን በጥራትና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በተቀናጀ መንገድ እየሰራ መሆኑን ገልጸው የጤና ዘርፍ ተመራቂዎችም ይህን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ታደሰ ሀምዳላ በበኩላቸው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በዕውቀትና በክህሎት የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ይህን ዕውን ለማድረግ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና በሌሎች መስኮች የተሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ኮሌጁ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ስድስት፣ በዲፕሎማ ደግሞ ዘጠኝ የትምህርት መስኮች ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝም በማመላከት።
ኮሌጁ ለመጀመሪያ ዙር በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ጨምሮ 561ተማሪዎችን ለሥልጠና ማብቃቱን አስታውቀዋል።
በኮሌጁ ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂው ምትኩ ወዳጆ ''ወደ ስራ ዓለም ስቀላቀል በቆይታዬ ያገኘሁትን ዕውቀት በመታገዝ ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ'' ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
''በማህበረሰቡን በታማኝነት፣ በርህራሄና በቅንነት በማገልገል ጤናው እንዲጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሌን አበረክታለሁ'' ሲልም አክሏል።
ከኮሌጁ ሚድዋይፍሪ ትምህርት ክፍል በማዕረግ የተመረቀችው ቤተልሔም ዮሐንስም በሙያዋ በመታገዝ በወሊድ ወቅት በሚከሰት የደም መፍሰስ የሚሞቱና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ እናቶችን ለመታደግ ጠንክራ እንደምትሰራ ገልጻለች።
በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የክልሉና የሀድያ ዞን የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።