ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ተኪ ምርት የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታትና የዘርፉን ሚና ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ሀዋሳ ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ተኪ ምርት የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት የዘርፉን ሚና ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሻሻሞ ቂሊሳ ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር አስተሳስሮ በመምራት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማነቃቃት የተወሰዱ እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጦች እያመጡ ነው ብለዋል።

በክልሉ 55 በተኪ ምርት የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሻሻሞ፣ ኢንዱስትሪዎቹ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በምግብና መጠጥ፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት እንዲሁም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።

''ኢንዱስትሪዎቹ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ምርታቸውን በስፋትና ጥራት እንዲያመርቱ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ለአብነትም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ የተለዩ ኢንዱስትሪዎችን በማቀናጀት ከውጭ የሚገቡ የተለያየ መጠንና አገልግሎት ያላቸውን ማሽነሪዎች በማምረት ለገበያ እያዋሉ መሆናቸውን ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በፋይናንስ አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት፣ በቦታ አቅርቦት እንዲሁም በሌሎች የመንግስትን እገዛ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የማስፋፊያ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የፋይናንስ አቅርቦት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት እንዲፈቱ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም "ኢንዱስትሪዎችን በክላስተር እንዲስፋፉ በማድረግ በተለይ የመሰረተ ልማት ችግሮቻቸውን በተደራጀ መንገድ መፍታት የሚያስችል የአሰራር ስልት ተነድፎ እንቅስቃሴ ጀምረናል" ብለዋል።

ኢንዱስትሪዎችን ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በማስተሳሰርና አቅማቸውን በመገንባት በጥራትና ዋጋ የተሻሉ ተወዳዳሪ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የ'ሪቨርስ ኢንጂነሪንግ' ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር በረከት መስፍን እንደገለጹት ድርጅታቸው የተለያየ መጠን ያላቸው በኮምፒዩተር የሚታዘዙ የመቁረጫ “ሲ.ኤን.ሲ” ማሽኖችን እያመረተ ነው።

ባመረቱት የመቁረጫ ማሽኖች ተጠቅመው የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የብረታ ብረት እና የእንጨት ውጤቶች በማምረት ለደንበኞቻቸው በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከውጭ ሲገባ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጀው ማሽን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ባልበለጠ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑንና ለአጠቃቀሙም በቂ ሥልጠና እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅታቸው በዓመት ከ30 በላይ ማሽኖችን የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ብቻ አምስት ማሽኖችን አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

መንግሥት የማምረቻ ሼድና የተለያዩ የገበያ ዕድሎችን እያመቻቸላቸው የሚገኝ ሲሆን፣ተጨማሪ የቦታ ጥያቄ አቅርበው በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

የ'ዛክ ግሪን ሶፍት' ፋብሪካ የምርትና ቴክኒክ ኃላፊ አቶ ዘላለም ብዙነህ ፋብሪካው ከዚህ በፊት ከውጭ ብቻ ይገቡ የነበሩ ሶፍት  (የመጸዳጃ ቤት ወረቀት) ምርቶችን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ በማምረት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው በአሁን ወቅት በግማሽ አቅም እያመረተ መሆኑንና በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር  በዓመት ከአንድ ሺህ ቶን በላይ ሶፍት እንደሚያመርት አስታውቀዋል።

''ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት እንዲገባ የማስፋፊያ ቦታ ጠይቀን በጥሩ ሂደት ላይ ነው'' ያሉት ኃላፊው፣ ''በቀጣይ ዓመት ምርታችንን ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፈን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመላክ አቅደን እየሰራን ነው'' ብለዋል።

በአብዛኛው ያገለገሉና ጥቅም ላይ የማይውሉ ወረቀቶችን በግብዓትነት የሚጠቀመው ድርጅት፣ በግብዓትነት የሚጠቀምባቸውንወረቀቶች ከየአካባቢው የሚያሰባስቡ  ማህበራትን ማደራጀቱንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም