ቀጥታ፡

በሮቤ-አሊ-ጋሠራ-ጊኒር መንገድ የተሰበረውን የብረት ድልድይ ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ሮቤ፣ ነሀሴ 25/2016 (ኢዜአ)፡- በባሌ ዞን በሮቤ-አሊ-ጋሠራ-ጊኒር መንገድ የተሰበረውን የብረት ድልድይ ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ። 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሮቤ-አሊ-ጋሰራ-ጊኒር መንገድ ላይ የሚገኘው ድልድይ በመሰበሩ ምክንያት ለጥቂት ቀናት ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆን ማስታወቁ ይታወሳል። 

ስለሆነም አሽከርካሪዎች መንገዱ ለትራፊክ ክፍት እስኪሆን ድረስ የሮቤ-ጎሮ-ጊኒርና ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

በአስተዳደሩ የባሌ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አመንሲሳ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በሮቤ-አሊ-ጋሠራ-ጊኒር መንገድ ላይ የተሰበረውን የብረት ድልድይ ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እያተደረገ ነው። 

በዌብ ወንዝ ላይ የተሰራው ይህ ድልድይ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ "ደምበል" በሚባል ከተማ አካባቢ ባለፈው ሀሙስ መሰበሩን ገልጸዋል።


 

በወቅቱ 450 ኩንታል ስንዴ ጭኖ በድልድዩ ላይ ለማለፍ የሞከረ ተሳቢ ብረት ድልድዩን በመደርመሱ መንገዱ መዘጋቱን ተናግረዋል።

የድልድዩ የመጫን አቅም 56 ቶን መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር አመንሲሳ፤ በድልድዩ ላይ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ተሽከርካሪና የጫናው ክብደት በድምሩ 81 ቶን እንደሚመዝን አስታውቀዋል። 

መንገዱን ለመጠገን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ክሬንና እስካቫተር ማሽኖችን ይዞ በቦታው በመገኘት ተግባራዊ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል። 

እስከ አሁን በተደረገው ጥረት የፊት የተሳቢው አካል የጫናው ስንዴ ሳይበላሽ የማንሳት ሥራ መከናወኑን ገልጸው፤ የተቀረውን የተሽከርካሪውን ተሳቢ አካል በማውጣት ወደ ጥገና ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ኢንጂነር አመንሲሳ እንዳሉት፣ የተሰበረውን ድልድይ ዳግም ለአገልግሎት ለማብቃት በአካባቢው ላይ የሚገኝ ተገጣጣሚ ድልድይ በማንሳት ለዚህኛው ቅድሚያ ሰጥቶ ጥገና ይከናወናል።

የጥገና ሥራውን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ድልድዩ ተጠግኖ ዳግም ለአገልግሎት እንዲበቃ በትዕግስት በመጠበቅ በአስተዳደሩ የተቀመጡ አማራጮችን እንዲጠቀም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም