ቀጥታ፡

አገርን በጀግንነትና በሰብዓዊነት የሚያገለግል የፖሊስ ሰራዊት ተገንብቷል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ):- ሕዝብና አገርን በጀግንነት በመጠበቅ በሰብዓዊነት የሚያገለግል የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት መገንባቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ኃላፊዎችና አባላት ዕውቅና ሰጥቷል።


 

የዕውቅና ሥነ-ስርዓቱ "የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጠብቀን ወንጀልን በመመርመር ፍትሕን ለማረጋገጥ እንሰራለን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመርሐ ግብሩ ባደረጉት ንግግር፤ ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው የነበሩ እስር ቤቶችን በመዝጋት የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር የምርመራ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

የወንጀል ምርመራ ሥርዓትን በማዘመን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን የተላበሰ ተቋም መገንባቱ በአገራዊና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ምስክርነት አግኝቷል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በጀግንነት በመጠበቅ በሰብዓዊነት የሚያገለግል እንዲሁም የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት መገንባቱን ነው የገለጹት።


 

የፌደራል ፖሊስ በለውጡ የወሰዳቸው እርምጃዎች፥ ሕዝቡ የፍትሕ ጥያቄዎቹ በሕግ አግባብ ምላሽ እንደሚያገኙ አመኔታ እንዲኖረው አድርጓል ብለዋል።

ፖሊስ ከወንጀል ምርመራ ስራዎች ባሻገር የአገር ውስጥና ድንበር ዘለል የጥፋት ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም ያቀዱትን የሽብር ተግባር ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመሆን ማክሸፉን ገልጸዋል።

በለውጡ ዓመታት በሙስና ተግባራት ላይ በተደረገ ጠንካራ የወንጀል ምርመራ ከ58 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና የመንግስት ንብረትን ማዳን ችለናል ነው ያሉት።

በወንጀል ምርመራ ሂደት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ የሚሰራ ጠንካራ ተቋም በመገንባት አስተዋፅኦ ላደረጉ የጠቅላይ መምሪያው ኃላፊዎችና አባላት ምስጋና አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ፤ በሽብር፣ በሙስና፣ በታክስና ጉምሩክ፣ በተደራጁና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦችን በአግባቡ መርምሮ ለሕግ በማቅረብ ስኬታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የጠቅላይ መምሪያው ኃላፊዎችና አባላት ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ውዝፍ የምርመራ መዛግብትን ወደ ፍርድ በማቅረብ ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ስኬታማ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የተጀመረው ቴክኖሎጂ መር የወንጀል ምርመራ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በፈጸሙት ወንጀል ብቻ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥርዓት መፍጠሩንም አስረድተዋል።

ለሠራዊቱ የስራ ኃላፊዎችና አባላት የሚደረገው ዕውቅና በየዓመቱ የተሻለ የስራ አፈፃፀም እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዚህ ዓመት ሽልማትም ለቀጣይ ስራ መነሳሳትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ዜጎች የዕለት ከዕለት ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ስኬታማ ሥራ መሥራቱ ተገልጿል።

ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝም ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ መርምሮ ለሕግ የማቅረብ ተልዕኮውን በሚገባ መወጣቱ በመድረኩ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም