"ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ላለበት ጨዋታ የአካል ብቃትና የቡድን ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው" አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ - ኢዜአ አማርኛ
"ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ላለበት ጨዋታ የአካል ብቃትና የቡድን ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው" አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታንዛኒያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የአካል ብቃትና የቡድን ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ገለጹ።
አሰልጣኙ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ስለቡድኑ አጠቃላይ ቅድመ-ዝግጅት አንስተዋል።
በዝግጅቱም የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ዝግ መሆን ተጨዋቾችን ከጨዋታ ውጪ ስላደረጋቸው የቡድኑ ከፊል ተጨዋቾች የአካል ብቃት ወርዶ እንደነበር አሰልጣኙ ተናግረዋል።
ስለሆነም ብሔራዊ ቡድኑ ሲዘጋጅ የቆየው የቡድን ሥራ ላይ ያተኮረ ሙሉ እንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ የተጨዋቾችን የአካል ብቃት የማስተካከል ሥራ እየሰራ ነው።
ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘቱ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም፤ በጨዋታው ላይ የታዩ የጎል አጨራረስ ድክመቶችን ለማስተካከል እስከ ጨዋታው ቀን ድረስ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በአራት ጨዋታ አንድ ጎል ማስቆጠሩ በአገሪቱ ሊግ የጎል አስቆጣሪ አጥቂዎች ቁጥር እንደተመናመነ ማሳያ እንደሆነ ነው ብለዋል።
ለዚህም ባለፉት ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው የሚጨርሱት አጥቂዎች የሌሎች አገር ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ነው ያሉት።
ስለሆነም ብሔራዊ ቡድኑን በግለሰቦች ላይ ሳይሆን እንደ ቡድን የሚያጠቃ አድርጎ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተነግሯል።
ለቡድኑ የአጥቂ መስመር አማራጭ ይፈጥራሉ ተብለው ጥሪ የተደረገላቸው አቡበከር ናስርና አቤል ያለው መጎዳታቸውም የቡድኑ የአጥቂ መስመር እንዲዳከም የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ሆኖም የንግድ ባንኩ አጥቂ አዲስ ግደይ ወደ ቡድኑ ተጠርቶ ልምምድ እያደረገ እንደሆነና የመጨረሻ 23 ተጨዋቾች ዝርዝር ውስጥ እንደሚካተት ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ 29 ከታንዛኒያ ጋር፤ ጷጉሜን 4/2016 ዓ.ም ደግሞ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዳሬሰላም ላይ ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።