ቀጥታ፡

ከፀሐይ በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል 25 አነስተኛ የገጠር ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው- የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ):- ከፀሐይ በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል 25 አነስተኛ የገጠር ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተገባደደ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ወልዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አማራጭ ኃይል ዘርፎች በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ ነው። 

በዚህም ከፀሐይ የሚመነጭ የኤሌክሪክ ኃይል (ሶላር ኢነርጂ) በመጠቀም የገጠር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

በተለይም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው  የሚገኙ የገጠር ከተሞችን በሚኒግሪድ ቴክኖሎጂ (ከቤተሰብ ፍጆታ በዘለለ ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚቀርብ የኤሌክትሪክ ኃይል) በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት 15 አነስተኛ የገጠር ከተሞች በሚኒግሪድ ቴክኖሎጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ለ100 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ነው አቶ ብርሃኑ የጠቆሙት።

በተጨማሪም በቅርቡ 25 አነስተኛ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።            

የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማኅበረሰቡ መብራት አገልግሎት ከማዋል ባለፈ ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የኃይል አቅርቦትን እንደሚያሻሽል አመልክተዋል።

በአነስተኛ ከተሞች የኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ተከላ መጠናቀቁን ጠቅሰው ቤት ለቤት የኤሌክትሪክ ማስገባት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።              

በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 345 ሺህ 520 ልዩ ልዩ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎች በማሰራጨት እስከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ።

በ2017 በጀት ዓመት የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በማሰራጨት ሕዝቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ፋይናንስ በማፈላለግና የግልን ዘርፍ በማሳተፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ ነው ብለዋል።  

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም