ቀጥታ፡

የስንዴ ልማት ሥራው ግብርናው ወደ ዘመናዊ እርሻ እያደረገ ያለውን ሽግግር እየመራ ነው

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦የስንዴ ልማት ሥራው በኢትዮጵያ ግብርናው ወደ ዘመናዊ እርሻ እያደረገ ያለውን ሽግግር እየመራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ መልካ ጀቢ ቀበሌ 1 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ኩታ ገጠም ማሳን ጎብኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ የኩታ ገጠም እርሻ፣ የተሟላ የግብዓት አቅርቦትና የመካናይዝድ እርሻ በስንዴ እርሻ በተሳካ ሁኔታ መተግበር ተችሏል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ በመኸር እርሻ ከ4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው የስንዴ እርሻ በኩታ ገጠም የታረሰ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ባስመዘገበችው ውጤታማ ሥራ፤አሁን ላይ የስንዴ ምርትን ከራሷ አልፋ ወደ ውጪ አገራት መላክ የጀመረች ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ እንድትይዝ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የስንዴ ልማት ሥራው ግብርናው ወደ ዘመናዊ እርሻ እያደረገ ያለውን ሽግግር እየመራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ እርሻ ሥራ የሽግግር ጉዞን እንደሚያቀላጥፍ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ መንገድ ጀምራለች ያሉት ሚኒስትሩ በዓመት ሦስት ጊዜ እያመረተች መሆኑንም ገልጸዋል።

የግብርና ሽግግር ለማሳለጥ ለወጪ፣ለተኪና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ እንደሚገኙም እንዲሁ።

የግብርና ሽግግር ለማፋጠንም በቴክኖሎጂ የታገዘና ሜካናይዜሽንን አስተራረስ ዘዴ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም