ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በማጠናከር የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሰራች ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን በማጠናከር የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የገቢና ወጪ ንግዷ ላይ መዛባት ከመኖሩ ባለፈ ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ ይነሳል።

ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችሉ በርካታ የምርት አይነቶችን የማምረት አቅም ቢኖርም ይህን አቅም አሟጦ በመጠቀም ወደ ውጪ መላክ ላይ ጉድለት መኖሩ በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ለዚህም እንደምክንያት ሲወሰዱ ከቆዩ ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነበር።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም መንግስት በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን ወደ ሙሉ ትግበራ አስገብቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዮሃንስ ፈንታ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ወደተሟላ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ለዲፕሎማሲ ስራዎች መጠናከር ሚናው የጎላ ነው።

ለአብነትም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን የበለጠ የሚያጠናክርና የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት ዕድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።

ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን በማምጣትና የአገር ውስጥ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ አይነተኛ ሚና እንዳለውም ነው የጠቀሱት።

በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ በውጭ ግንኙነት ሥራዎች የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራትን በዋና ተልዕኮነት እየፈጸመ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር ዮሐንስ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት በመስራቷ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

ይሁንና የሚመረተውን ምርት የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ላይ ውስንነቶች ይታያሉ ነው ያሉት።

ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን ምርቶች በውጭ ሀገራት የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገቢራዊ ከመደረጉ በፊት በነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ህገ-ወጥ ንግድ የከብት ስጋን ወደ ውጪ መላክን እስከማቆም ደርሰው እንደነበር የሚያስታውሱት የሃላላ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ አምራችና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ከሊፋ ሁሴን ናቸው።


 

ሰብሳቢው እንደሚሉት በትይዩ ገበያው የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ልዩነት የወጪ ንግዱ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ቆይቷል።

የገበያ መዳረሻዎች መጥበብና የተወዳዳሪነት አቅም ማነስ ዘርፉ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሬ እንዳያስገኝ ስለማድረጉም ነው ያነሱት።

በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ወደ ተሟላ ትግበራ ሲገባ የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የተደረገው ለውጥ በዘርፉ መነቃቃትን መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋትና ምርትን በተወዳዳሪነት ለመሸጥ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ዮሐንስ እንደሚሉት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ተግባራዊ መሆን የወጪ ንግዱን በማሳደግ የተሻለ ገቢ እንዲገኝ ዕድል ይፈጥራል።

ሚኒስቴሩም ለዚህ የሚሆን እቅድ በማዘጋጀት እያንዳንዱ ሚስዮን የገበያ አማራጮችን የማስፋት ስራ እንዲተገብር ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የተሻለ አፈጻጸም እንደሚኖር አንስተዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞችን በማዘጋጀት እንዲሁም አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም