ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- የኢንቨስትመንት ኮሚሽን

ሚዛን አማን ፤ነሐሴ 25/2016 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ተወዳዳሪና ተመራጭ  ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት መንግሥት ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ በርካታ ለውጦችን ማድረጓን አውስተው፣ በዚህም በዘርፉ አሳሪ የሆኑ ህጎችን በማሻሻል ውጤታማ ለመሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የአገሪቱን ጸጋዎች በአግባቡ በማስተዋወቅ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ይህን ለማጠናከር በየአካባቢው ያሉት ጸጋዎች አቅም እንዲወጣ ይሰራል ያሉት አቶ ዳጋቶ፣ ጥረቱን በማቀናጀት ውጤታማ ለመሆን መስራት ይገባናል ብለዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር/ኢ/ር) የክልሉ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ  የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም በክልሉ ያሉትን አማራጮች በአግባቡ በመለየት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላትን በተቀላጠፈ መልኩ ማስተናገድ የሚችሉባቸውን አሰራሮች ማመቻቸቱን አስረድተዋል።

በክልሉ ያሉትን አማራጮች ተጠቅመው ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ በክልሉ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን የላቀ ሚና ለማጠናከርም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም