የክልሉ ዲያስፖራ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት - ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ዲያስፖራ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት - ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን
አዳማ ፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ የክልሉ ዲያስፖራ የመንግስት አቅም በማይደርስበት አካባቢዎች የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሳዓዳ አብዱረህማን አስገነዘቡ።
በኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር በአዳማ ከተማ የተገነባው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ተመርቆ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ተረክቦታል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ ሀገርን ለማልማት የተቀናጀ ጉልበት፣ ዕውቀትና ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚሁ መነሻነት የኦሮሚያ ክልል መንግስት የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራ በልማትና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ እያበራታታ መሆኑን አንስተዋል።
በዚሁም መሰረት በህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒት፣ በትምህርት ቁሳቁስ፣ በማህበራዊ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ቡኡራ ቦሩ የተሰኙ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን አስታውሰው በዲያስፖራ ተሳትፎ ተገንብቶ የተመረቀው ይህ ትምህርት ቤት የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆነ አስረደተዋል።
በቀጣይም የክልሉ ዲያስፖራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዘርፎች ተሳትፎውን በማጠናከር የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው በበኩላቸው አገልግሎቱ ዲያስፖራው ያለውን አቅም ለአገሩ እንዲያውል የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር በተሻለ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ዲያስፖራው አገሩን እንዲያግዝ አመች ሁኔታ መኖሩንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎች ያሏት በመሆኑ የዲያስፖራው ተሳትፎው እንዲጠናከር ይደረጋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የዲያስፖራ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አሚን ጁንዲ፣ የክልሉ ዲያስፖራ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ግንባታን እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ በአዳማ ከተማ ተገንበቶ የተመረቀው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትም አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ዲያስፖራው የአስተሳሰብና አመለካከት ልዩነት ሳይገድበው ክልሉን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
በኳታር፣ ኢራንና የመን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ፣ ዲያስፖራው በጉልበቱ፣ በዕውቀቱና በገንዘቡ አገሩን እንዲያግዝ የማነሳሳት ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ዲያስፖራው የልማት ሀይል መሆኑን በአዳማ ከተማ የተገነባው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አንዱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
ዲያስፖራው በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አሻራቸውን እንዲያሳርፍ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ ናቸው።
በዚህም ዲያስፖራው ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተሳትፎ ባለፈ በኢንተርፕሩነር ሽፕ፣ ክህሎት ልማትና አቅም ግንባታ ወጣቶችን ማገዝ እንደሚገባው ጠይቀዋል።
በከተማዋ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 31 ፕሮጀክቶች በኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር እየተገነቡ መሆኑንም አክለዋል።