የኢቢሲ ስቱዱዮ በአሶሳ ከተማ በአጭር ጊዜ መገንባት የክልሉ መንግስት ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው - ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢቢሲ ስቱዱዮ በአሶሳ ከተማ በአጭር ጊዜ መገንባት የክልሉ መንግስት ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው - ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ
አሶሳ፣ ነሃሴ 25/2016 (ኢዜአ)፦ የኢቢሲ ስቱዱዮ በአሶሳ ከተማ በአጭር ጊዜ መገንባት የክልሉ መንግስት ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በአሶሳ ያስገነባው ስቱዲዮ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኢቢሲ አመራር አባላትና ሰራተኞ በተገኙበት ተመርቋል።
በዚሁ ጊዜ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፣ የኢቢሲ ስቱዱዮ በአሶሳ ከተማ በአጭር ጊዜ መገንባት የክልሉ መንግስት ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሰጠውን ትኩረት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ኢቢሲ በተለያዩ አካባቢዎች ለህዝብ ቀርቦ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ስራም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ጅምሩ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሐሰን በበኩላቸው የኢቢሲ አሶሳ ስቱዲዮ የክልሉን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች በፍጥነት እና በጥራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ሚዲያው የክልሉን ህዝብ ባህል እና እሴት እንዲሁም ሁለንተናዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል።
ክልሉ የብዝሃነት ማሳያ፤ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ኢቢሲ የክልሉን ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው ስቱዲዮውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ላደረገላቸው ትብብር አመስግነዋል።
ኢቢሲ በቀጣይ በአዳዲስ ይዘቶች ወደ ህብረተሰቡ ለመድረስ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።