ቀጥታ፡

በቅርቡ ሥራ የጀመሩት የሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኅብረተሰቡ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ የሚያጠናክሩ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ በቅርቡ ሥራ የጀመሩት የታላቁ  ሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኅብረተሰቡ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የሕዳሴ ግድብ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የወንዝ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውኃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜኪ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ ጀምረዋል ብለዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ሥጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውኃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ የተመዘነና የተመጣጠነ የውኃ ልቀት ግብርናን፣ ኃይል የማመንጨት ሥራን፣ በቀጠናው ያለ የኃብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማልም ነው ያሉት። 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግድቡን ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ለስኬት እያበቁት ነው። 


 

ግድቡ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ያለው መሆኑ በራስ አቅም ጠንክሮ በመሥራት አገሪቱን ከድኅነት ማውጣት እንደሚቻል የሚያመላክት ብሔራዊ ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።  

በቅርቡ ሥራ የጀመሩት ሁለት የግድቡ ተርባይኖች ኅብረተሰቡ አሁን ለግድቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎና ተነሳሽነት ይበልጥ ከፍ የሚያደርገው መሆኑን ገልፀዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ ግንባታ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ከሕዝብ የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል። 

በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ሰፋፊ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች እንደሚከናወንም አንስተዋል።

ግድቡን ለማጠናቀቅ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በተለያዩ ክልሎች  ዋንጫዎችን በማዘዋወር ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በዲጂታል መተግበሪያ አስተዋጿቸውን እንዲያጠናክሩ መደረጉን ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም