ቀጥታ፡

ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ዘላቂ ሰላም እውን የሆነባት አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ):- ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ዘላቂ ሰላም እውን የሆነባት አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስገነዘበ።

ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።

ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በማለም የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋሙን አስታውሰዋል።


 

በዚህም ኮሚሽኑ ተሳታፊ አካላትን ከመምረጥ ጀምሮ አሁን እስከሚገኝበት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት መድረሱን ጠቅሰዋል።

በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ምክክር በማድረግ መሳተፋቸውን ገልጸው፤ እስከአሁን ያለው ሂደት ውጤታማ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በየጊዜው እየተስተዋሉ ከሚገኙ ችግሮች በመውጣት ሰላማዊ አገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ በምክክር ሂደቱ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበትም አስረድተዋል።

በሆሳዕና ከተማ በተጀመረው የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ተሳታፊዎችም አካታችነት፣ ግልፀኝነት፣ አሳታፊነትንና ተዓማኒነትን መሰረት በማድረግ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ በሚኖረው የስድስት ቀናት ቆይታ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተመራጮች እና ባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብና ክልላዊ የምክክር ጉባኤውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም