የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በምርምር ይደግፋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በምርምር ይደግፋል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የሰብል ምርታማነትን በመጨመር በምግብ እራሷን ለመቻል የምታከናውነውን ተግባር በምርምር እንደደሚደግፍ የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) አስታወቀ።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የግብርና እድገትን ለማፋጠን እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጣር በ2006 ዓ.ም መመስረቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ጥምረቱ ከዘር ብዜት፣ የአፈርን ጤናማነት ከማስጠበቅና ከግብርና ጋር የተያያዙ የገበያ ዕድሎችን በማመቻቸት ረገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ይነገራል።
በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ፎረም በማቋቋም ቀጣናዊ ትስስርን ለማዳበር የሚያግዝ ስራ እንደሚያከናውንና በኢትዮጵያም በተለያዩ የግብርና ልማት ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይገለጻል።
የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይሔነው ዘውዴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው።
በተለይም ለስንዴ፣ የቅባት እህሎች፣ ሩዝና ለሌሎች የሰብል አይነቶች ቅድሚያ በመስጠት ከተረጅነት ለመውጣት እያከናወነች ያለችው ተግባር ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያላትን ሰፊ እድል ያመለከተ ነው።
ኢትዮጵያ ለነዚህ ሰብሎች ቅድሚያ በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ለነደፈችው ፖሊሲና ስትራቴጂ አግራ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በአግራ የምርት ዘመን ማለትም እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ2023 እስከ 2027 የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ለሰጣቸው ሰብሎች በምርምርና በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ለማድረግ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ምርጥ ዘሮችን በስፋት በማምረት ለአርሶ አደሮች ለማዳረስ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ የነዚህን ሰብሎች ምርታማነት መጨመር በምግብ እራስን ለመቻል ብቻ ሳይሆን ለወጪ ንግድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።
አግራ ከግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በምግብ እራስን ለመቻል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በማዘጋጀትም በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ጨምረዋል።
ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የተቋቋመው ከ18 አመት በፊት ሲሆን በግብርና ልማት፣ ምርምር፣ በሰው ሃይል ልማትና በሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።