የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ የሥራ ኃላፊዎችና አባላቱ ዕውቅና ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ የሥራ ኃላፊዎችና አባላቱ ዕውቅና ሰጠ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ የሥራ ኃላፊዎችና አባላት ዕውቅና ሰጥቷል።
የዕውቅና መርኃ ግብሩ "የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጠብቀን ወንጀልን በመመርመር ፍትሕን ለማረጋገጥ እንሰራለን" በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታና የደኅንነት ዘርፍ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የአገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ የፍትሕ፣ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በመርኃ ግብሩ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በበጀት ዓመቱ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዜጎች ያለ ምንም የፀጥታ ሥጋት የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲመሩ ወንጀልን በመከላከል ስኬታማ ሥራ መሥራቱን ገልጿል።
ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝም ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ መርምሮ ለሕግ የማቅረብ ተልዕኮውን በሚገባ በመወጣትም የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የተሳካ ሥራ በበጀት ዓመቱ ማከናወኑን መግለጹ ይታወሳል።