ቀጥታ፡

በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2016 (ኢዜአ):- በፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ።

ውድድሩ ከነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ እየተከናወነ ይገኛል።

በውድድሩ ላይ ከ184 አገራት የተወጣጡ ከ4000 በላይ አትሌቶች በ22 የስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በውድድሩ በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታዎች በስድስት አትሌቶች ተወክላለች።

ከቀኑ 6 ሰዓት ከ11 ላይ 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው የስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም በሚደረገው የ1500 ሜትር የእጅ ጉዳት (T-46 ምድብ) ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ገመቹ አመኑ ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል።

አትሌት ገመቹ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በጃፓን ኮቤ በተካሄደው 11ኛው የዓለም ፓራአትሌቲክስ ሻምፒዮና የ1500 ሜትር የእጅ ጉዳት (T-46) ፍጻሜ 3 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ከ61 ማይክሮ ሴኮንድ አራተኛ መውጣቱ ይታወቃል። የገባበት ጊዜም የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።

ገመቹ ከሶስት ዓመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ተወዳድሮ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ13 ላይ የ1500 ሴቶች የጭላንጭል (T-13) ፍጻሜ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ትወዳደራለች።

አትሌት ትዕግስት እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ተሳትፋ በውድድሩ ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቷ የሚታወስ ነው።

ትዕግስት በጃፓን ኮቤ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው 11ኛው የዓለም ፓራአትሌቲክስ ሻምፒዮና 1500 ሴቶች ጭላንጭል ፍጻሜ 4 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ90 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። የገባችበት ጊዜም የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው።

በፍጻሜው ውድድር ላይ 11 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

አትሌት ያየሽ ጌቴ እና አትሌት ይታያል ስለሺ ይግዛው በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

አትሌት ያየሽ በ1500 ሴቶች በአይነስውር (T-11 የውድድር ዘርፍ) ነገ ለፍጻሜ ለማለፍ የማጣሪያ ውድድሯን ታደርጋለች።

አትሌት ይታያል በ1500 ወንዶች አይነስውር ጭላንጭል (T-11) ፍጻሜ ለመሳተፍ ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም የማጣሪያ ውድድሩን ያከናውናል።

በውድድሮቹ ላይ አትሌቶቹን የሚደግፉ ሁለት አሯሯጭ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ።

17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የአካልና የስነ አዕምሮ ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የባለ ብዝሃ ስፖርቶች ውድድር ነው።

የፓራሊምፒክ ውድድሩ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም