በአማራ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 25/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ድጋፍ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጹ።
የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ ፤ ግድቡን ለፍፃሜ ለማብቃት እየተደረገ ባለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ክልሉ የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አራቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው የኢትዮጵያን ዕድገት እንዲፋጠንና የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ትውልዱ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት የልማት ተምሳሌትነቱን በተግባር በማሳየት ታሪክ ሰሪ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።
ለዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከባለሃብቶችና ሌሎች በቦንድ ግዥና በልገሳ 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ ውስጥ ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ 900 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከቦንድ ግዥ በመሰብሰብ መልካም ጅማሮ መኖሩን ጠቅሰዋል።
ግድቡን ለፍፃሜ በማብቃት መላው ህዝብ የጀመረውን የቦንድ ግዥ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ህዝቡ ከቦንድ ግዥ በተጨማሪ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና ችግኝ ተከላም አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ አቶ ተናኘ አብራርተዋል።
የባህር ዳር ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ አቶ ሞላ ካሴ በሰጡት አስተያየት፤ ‘‘በይቻላል መንፈስ የግድቡ ግንባታ ለፍፃሜ ተቃርቦ በማየቴ ደስታዬ ወደር የለውም’’ ሲሉ ገልጸዋል።
በመላ ኢትዮጵያዊያን አንድነትና ትብብር የተገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከአድዋ የነፃነት ታሪክ ቀጥሎ ለአፍሪካ የልማት ተምሳሌት ማሳያ ፕሮጀክት ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
''ይህም በቀጣይ አገሪቱ በኢኮኖሚ የፈረጠመች እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ እያንዳንዳችን የልማቱ ትሩፋት ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል'' ብለዋል።
''እኔም ከወር ደሞዜ ቦንድ በመግዛትና ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በመሳተፍ አሻራዬን እያሳረፍኩ እገኛለሁ'' ሲሉ ተናግረዋል።
ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የክልሉ ህዝብ ቀደም ሲል በቦንድ ግዥ፣ በልገሳ፣ በተፋሰስ ልማትና በችግኝ ተከላ የተከናወነው ስራ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋፅኦ ማድረጉም ተመልክቷል።