በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ ኢትዮጵያ የምትወዳደርባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ ኢትዮጵያ የምትወዳደርባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ):- ዛሬ ፍጻሜውን በሚያገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እስከ አሁን 7 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በሻምፒዮናው የመጨረሻ ቀን ውሎ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ የሴቶች የ1500 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። አትሌት ሳሮን በርሄና አትሌት ፅጌ ተሾመ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ሳሮን በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ሺያሜን በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።
ሳሮን በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።
አትሌት ፅጌ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ከ40 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።
በፍጻሜው ውድድር ላይ 15 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ15 የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ ይደረጋል። አትሌት ኃይሉ አያሌውና አትሌት በሪሁን ሞገስ ይወዳደራሉ።
አትሌት ኃይሉ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 8 ደቂቃ ከ47 ሴኮንድ ከ60 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገቡ ይታወቃል።
አትሌት በሪሁን በዘንድሮው ሻምፒዮና በማጣሪያ ውድድር ላይ 8 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ92 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
ከሌሊቱ 8 ሰዓት ከ5 ላይ የወንዶች 1500 ሜትር ፍጻሜ ይከናወናል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ብቸኛ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ነው።
አብዲሳ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በስፔን በተከናወነ ውድድር 3 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ37 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
አትሌቱ በዘንድሮው ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ወንዶች የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወቃል።
የ1500 ሜትር ፍጻሜ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ተሳትፎ የምታደርግበት የመጨረሻ ውድድር ነው።
ኢትዮጵያ በፔሩ ሊማ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና እስከ አሁን 4 የወርቅ፣ 2 የብርና 1 የነሐስ በአጠቃላይ 7 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ከነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ይጠናቀቃል።