አረንጓዴ አሻራ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሥራ ዕድል ፈጠራ

በክፍሌ ክበበው (ኢዜአ)

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በ2011 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በዚሁ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 23 ሚሊዮን ህዝብ ተሳትፎ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በዚህም በመርሃ ግብሩ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በሕዝብ ተሳትፎ ለአራት ዓመታት በተካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል በስኬት ተጠናቋል።

የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረው “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሆን፤ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እ.ኤ.አ በሐምሌ 2017 በሕንድ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ በ12 ሰዓታት 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወስን ኢትዮጵያ መረከብ ችላለች።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከመጀመሪያው ምዕራፍ አንስቶ ከዓመት ዓመት የኅብረተሰቡን ተሳትፎን እያሳደገ በስኬት እየተጠናቀቀ ከዚህ ደርሷል።

በ2015 ዓ.ም መተግበር በጀመረው በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች ትኩረት እንደተሰጠ መረጃዎች የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ከዚህም ባሻገር ችግኞችን ለጎረቤት አገራት በመስጠት ኢትዮጵያ ችግኞችን በመትከል ዓለም ዓቀፍ ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቅረፍ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ አርዓያነቷን ያሳየችበት መሆኑ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የመሰከሩለት ሀቅ ነው።

በዘንድሮው ለስድስተኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ሥራው በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዕለቱ አብስረዋል።

ይኸው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ነሐሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም “የምትተክል ሀገር፤ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ለጥምር ደን፣ ለምግብነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የመትከል ለአረንጓዴ ልማት እና ለአረንጓዴ አካባቢ መላ ኢትዮጵያውያን ለትውልድና ለዓለም የሚተርፍ በስኬት ተጠናቋል።

“ያሰብነውን ሳናሳካ ጀምበር የሚጠልቅብን አይደለንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ  የተሳተፉ  29 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በ318 ነጥብ 4 ሄክታር በሚሸፍኑ ሥፍራዎች ላይ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስካሁን ባለው ሂደት 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከልናቸውን ችግኞች ሲደመሩ ወደ 40 ቢሊዮን ይደርሳሉ ፡፡

ይህ ስኬት ለአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን ለመጠበቅ፣ የአፈር መራቆትን ለመመከት እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲሁም ምድራችንን አረንጓዴ ለማልበስ እና ልምላሜን ለመመለስ ሳንበገር ሰርተናል ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ለምግብነት፣ ለመድሐኒትነትና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና የተቀረው ደግሞ ለውበትና ለአከባቢ ጥበቃ የሚውል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

እንደሳቸው ገለጻ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረትን በማሻሻል እና ብዝሃ ህይወትን በመደገፍ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን፤ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዉያንን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚያስማማ ነው።

የተተከሉት ችግኞች ሲጸድቁ ስነምህዳሩን ከማሻሻል፤ የአፈር መሸርሸርና መከላትን ከመከላከል እንዲሁም የሥራ ዕድልን ለበርካቶች ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው። የተጎዳና የተራቆተ አካባቢ ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አካባቢያቸውን ለምግብነት እና ለአየር ንብረት ለውጥ በደን ለማልበስ በሚደረግላቸው ቴክኒካዊ ድጋፍ ተጠቅመው አኗኗራቸውን ለመለወጥ ያስችላል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የሚገኙ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ምህዳር እንዲፈጠር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ገባሮች እንዲጠናከሩ እያደረገ መሆኑን እና ጎርፍን በመከላከል፣ የአፈር መከላትን በማስቀረት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራ እና የተፋሰስ ልማቱ በተራቆቱ አካባቢዎች የደን ሀብት መልሶ እንዲያገግምና  ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው እንዲመነጨናና የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያገዘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ዓመታት ችግኞች በመተከላቸው የአፍሪካ ኩራት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚጠበቀው በላይ ውሃ መያዙን ገልጸው፤ ግድቡን ከደለል ለመታደግ፣ በቂ ዝናብ፣ ምግብና መድሃኒት ለማግኘት በዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች በቀጣይ ችግኞችን  አብዝቶ መትከል ይጠበቅብናል፣ ይህም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮችም በቂ ውሃ እንዲያገኙም ያስችላል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፈር ደለል እንዳይሞላ፣ በአካባቢው ሥነ ምህዳሩን ለመጠበቅ እና ረጅም ዓመት አገልግሎት መስጠት እንዲችል በተፋሰሱ ዙሪያ ችግኞች በቀጣይነት መትከል ይገባል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በተፋሰስ ልማት ምንጮችን በማጎልበት እየለማ ያለው የውሃ ሀብትም የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ ተጨማሪ አቅም ሆኗል። በግብርና ልማት  በአገር አቀፍ ደረጃ በበጋ መስኖ ልማት የበጋ ስንዴ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዲጨምር በማድረግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የሥራ ዕድልን በመፍጠር የበከሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተፋሰስ ልማት እየለማ ያለው የውሃ ሀብትም የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ ተጨማሪ አቅም ሆኖ ለግብርና ልማት እና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለጎረቤት አገራትም ጭምር የሚተርፍ ሆኗል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ትንበያዎች ያመላክታሉ።እ.ኤ.አ. በ 2012 የተመሰረተው እና በብሪታኒያ  ዕርዳታ  የሚደገፈው  ኤፍኤስዲ  አፍሪካ  ለወደፊቷ  አፍሪካ ፋይናንስን  ለመስራት የሚተጋ የልማት ኤጀንሲ ባወጣው አዲስ የትንበያ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. በ2030 ከሦስት ሚሊዮን በላይ ቀጥተኛ ሥራዎችን መፍጠር የሚያስችል ነው።

ኤፍኤስዲ አፍሪካ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ በአፍሪካ የፋይናንስ ገበያዎች ውስጥ ያሉ የሥርዓት ተግዳሮቶችን ለመፍታት መጠነ ሰፊ እና የረጅም ጊዜ ለውጥን ለመፍጠርን  ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነው።ባለፈው ወር መጨረሻ ይፋ ባደረገው ትንበያ በ2030 አሥራ ሁለት "አረንጓዴ" ንዑስ ዘርፎች ያለውን አዲስ ቀጥተኛ የስራ ዕድል የሚተነብይ "በአፍሪካ የአረንጓዴ ሥራዎች ትንበያ " በሚል ርዕስ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ዘገባ የፈጠራ ሥራዎችን ከሚደግፈው ሾርትሊስት (Shortlist) ከተባለው ተቋም ጋር አሳትመዋል።

እ.አ.አ በ2030 በአህጉሪቱ እስከ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ በተለይም ከአብዛኛዎቹ በፀሐይ ኃይል አዳዲስ ቀጥተኛ ሥራዎች እንደሚፈጠሩ በትንበያ ሪፖርቱ አመልክቷል።በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በዋና ዋና የአረንጓዴ እሴት ሰንሰለቶች ማለትም በካርቦን ንግድ፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማት እና በታዳሽ ኃይል ያለውን የሰው ኃይል ፍላጎት ለመጀመሪያ ጊዜ በጥልቀት የተተነተነው ጥናቱ ለአምስት አገሮች፤ ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያተኮረ ዝርዝር ትንበያ አውጥቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ 33 ሺህ ሥራዎች ቀዳሚ ቀጣሪ እንደምትሆን በተቋማቱ ጥናት ተካቷል። በዚሁ ጥናት ከ377 ሺህ በላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ የስማርት ግብርና ቴክኖሎጂ ልማት እና ግብርና እና ተፈጥሮ እስከ 700 ሺህ የሚደርሱ ሥራዎችን እንደሚፈጥርም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ለመሆን ጠንካራ ቁርጠኝነትን እያሳየች መሆኑን ኤፍኤስዲ አፍሪካ (FSD Africa) በዘገባው ጠቅሷል።

በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የካርቦን ኢነርጂ ልማትን በማረጋገጥ፣ ሰፊ የደን ክምችቷን በመጠበቅ እና ግብርናዋ የአየር ንብረትን የመለማመድ እና የመቋቋም አቅምን ማሳደግ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

ኢትዮጵያ ሀገራችን በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተገኘበት እና የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት የታየበት እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውና አበርክቶው የላቀ በመሆኑ ኢትዮጵያዉያን ይህንን እየዳበረ የመጣውን በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ፣ የለማች፣ ያደገችና የበለጸገች አገር ለተተኪው ትውልድ የማስረከቡን ባሕል በበለጠ ሊያጸኑት ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም