በኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን ጎበኘ - ኢዜአ አማርኛ
በኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን ጎበኘ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን በሰንዳፋ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን ዛሬ ጎብኝቷል።
ዋና ፀሐፊው ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ እያደረገ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ፖሊስነት የአገርን ክብርና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት የሚከናወን ሳይንሳዊ ሙያ በመሆኑ ለውጡን የሚያግዝ የተማረ የሰው ኃይል ለማሟላት ባለሙያዎችን የማብቃትና የማሰልጠን ስራን ተጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኝ አንጋፋ የፖሊስ የትምህርትና ስልጠና ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት የአፍሪካ አገራት በሰላምና መረጋጋት ላይ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ከማገዝ ባለፈ ለፖሊስ መኮንኖችም የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና ሊፈጠሩ የሚችሉ የወንጀል ስጋቶችን እንዲሁም ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPAPP) በማበልፀግ ወደ ስራ ማስገባቱን አስታውሰዋል።
የጎረቤት አገራትም መተግበሪያውን እንደ ተሞክሮ በመውሳድ ለሕዝባቸው የዘመነ የፖሊስ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉም ነው ኮሚሽነር ጀነራሉ ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሚሽነር ጌቱ ተክለዮሐንስ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት በርካታ ዓመታት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት የፖሊስ አመራርና አባላት ትምህርትና ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ኩራት የሆነ የፖሊስ ተቋም ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፋ ከፍተኛ አመራሮች ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ እያከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታና ሌሎች አገራትም ልምድና ተሞክሮ ሊወስዱበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን በዩኒቨርሲቲው እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን መጎብኘቱን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።