ቀጥታ፡

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል እና ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የስፖርት የሕክምና ማዕከል ለመክፈት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ) ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል እና ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የስፖርት የሕክምና ማዕከል መክፈት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርመዋል።

ማዕከሉ ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የነፃ ምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ላለፉት ዓመታት ተጨዋቾችን በነፃ በመመርመር በአጋርነት ሲሰሩ የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል የስፖርት ክሊኒክ ለመክፈት ውል ተፈራርመዋል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤት ዳዊት ኃይሉ እንዳሉት የስፖርት ክሊኒኩ ለብሔራዊ ቡድኑ የቅድመና ድህረ ጉዳት ነጻ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው "በሜዲካል ዲፓርትመንት አማካኝነት ስምምነት በማድረግ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሲጎዱ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት ሲመረመሩ ነበር።


 

ይህ በገንዘብ ሲተመን ብዙ ዋጋ የሚያስወጣ ይሆን ነበር፤የዛሬው ስምምነት ይህንን የሚያስቀር ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የነፃ ምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጥ የማዕከሉ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ኃይሉ  በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ነፃ የሕክምና አገልግሎቱ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ፣ የራጅ፣ ኢንዶስኮፒና በማዕከሉ የሚሰጡ ሌሎች የምርመራ አገልግሎቶች የሚያካትት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከመንግሥት የሕክምና ተቋማት በሐኪም ምርመራ ታዞላቸው በአቅም ውስንነት ምርመራውን ለማድረግ ያልቻሉ ወገኖቻችን የነፃ ሕክምናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አክለዋል።

ማዕከሉ ባለፉት 14 ዓመታት መሰል ነፃ የሕክምና ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ከ54 ሺህ በላይ ወገኖች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት ዶክተር አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት አበረታች ውጤት እያሳየ እንደሆነ አስታውሰዋል።


 

የጤና ተቋሙ ለ15ኛ ጊዜ እየሰጠው ያለው ጳጉሜን ለጤናን ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚበረታታና ለሌሎች የሕክምና ተቋማትም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

የነፃ የሕክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ከየትኛውም አካባቢ የሚመጡ ሰዎች በስልክ ቁጥር 9888 ወይም በ0940 040404 እንዲሁም  0940101010  መጠቀም እንደሚችሉ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም