ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልል የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች አጀንዳዎች የሚያደራጁላቸው ወኪሎችን መረጡ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- የሲዳማ ክልል የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች አጀንዳዎቻቸውን የሚያደራጁላቸው ወኪሎቻቸውን ዛሬ መምረጣቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ እየተደረገ በሚገኘው የምክክር መድረክ ተወካዮች ከነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ለሶስት ቀናት ከወከሉት ማህበረሰብ ይዘውት በመጡት አጀንዳ ላይ ሲወያዩና ሲያደራጁ ቆይተዋል።

የማህበረሰብ ክፍሎች ወኪሎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማህበራትና ተቋማት፣ከመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ከታዋቂ ግለሰቦች ወኪሎች ጋር ሆነው የሚወያዩላቸውን ወኪሎች መርጠዋል።

እያንዳንዳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ስድስት፣ በድምሩ አስሩ የማህበረሰብ ክፍሎች 60 ወኪሎችን ዛሬ መምረጣቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

የተመረጡት 60 የሕብረተሰብ ወኪሎች ከነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምረው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሆነው በሲዳማ ክልል አጀንዳዎች ላይ እንደሚመካከሩ ገልጿል።

አምስቱ ባለድርሻ አካላት የሚያደራጇቸው አጀንዳዎች ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በዋናው መድረክ ከቀረቡ በኋላ የሲዳማ ክልል አጀንዳ ሆነው ኮሚሽኑ ይረከባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም