ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያው አምራች ዘርፉን ለማነቃቃትና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስችላል

ሀዋሳ ፤ነሀሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአምራች ዘርፉን ለማነቃቃትና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ  ሰላማዊት ካሳ አስታወቁ።

በሚኒስትር ዴኤታዋ የተመራ የጋዜጠኞች ቡድን የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።


 

ሚኒስትር ዴኤታ  ሰላማዊት ካሳ ከጉብኝቱ በኋላ እንደገለጹት መንግስት አምራች ዘርፉን ለማበረታታትና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል።

ከዚህም ውስጥ አዲስ ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሀገሪቱ የአምራች ዘርፉን ለማነቃቃትና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደሀገር ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትልቅ ውጤት እንደተገኘበት የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታዋ አዲስ የተተገበረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ለመስራት እንዲችሉ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን አመላክተዋል።

በዚህም ሀገሪቱ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደምትሆንና በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኢንዱስትሪያል ፓርኮችን የስራ እንቅስቃሴ ከማሳደግ አንጻርም ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጨማሪ ሀይል ማመንጨት መጀመሩ በአምራች ዘርፉ የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችልና በመንግስት በኩል እየተሰሩ ካሉ አበረታች ተግባራት አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጪ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙ የኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ በፓርኩ ያለውን እንቅስቃሴም እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በፓርኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረን ተመልክተናል፤ እየተከተሉት ያለው አሰራር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ነው ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ዘርፉ እድገት 10 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ወደ 12 በመቶ ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል፤ በተለይ የጨርቃ ጨርቁን ኢንዱስትሪ ከነበረበት 64 በመቶ ወደ 75 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ጥራት ያላቸውን አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች መሳብ ብቻ ሳይሆን ከገቡ በኋላ ዛሬ የተመለከትናቸውን አይነት ትልልቅ ፋብሪካዎች አምራችነታቸውንና ለገበያ የሚያቀርቡትን ምርት መጠን ማሳደግ አስፈላጊ ነው  ሲሉም አክለዋል። 

ከዚህም ባሻገር የአምራቾችን ትስስር መፍጠር ሌላው ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው የአንዱን አምራች ምርት ሌላው ወስዶ በግብዓትነት እንዲጠቀም ከማድረግ አንጻር በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በማህብረሰቡ ውስጥ ያለውን የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድ ከፍ እንዲል ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በትብብር የሚሰራበት እንቅስቃሴ የሚጠናከር ይሆናል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚጠበቅባቸው ተግባራት አንዱ ከፍሳሽ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር መፍታት መሆኑን ጠቁመው ከዚህ አንጻር በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በጉብኝቱ ፓርኩ ብዙ አቅም እንዳለውና የአካባቢውን ማህበረሰብ መጥቀም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን በበኩላቸው እንዳሉት የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያዎች ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ተፈላጊነቱን እያሰፋ ያለ ፓርክ ነው።

ፓርኩ ለሀገር ከሚያስገኘው የውጪ ምንዛሬ በተጨማሪ በእውቀትና ክህሎት ሽግግር ዙሪያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩ የአገዋ እድል የተቋረጠ ቢሆንም በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ ገበያ ተፈላጊነቱን ከማሳደግ ባለፈ በብሪክስ ሀገራት ምርቱን እየሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ወደ ውጪ ከላካቸው ምርቶች 44 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት እንደቻለ አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ አሸናፊ በበኩላቸው እንዳሉት ፓርኩ 24 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ለአካባቢ ጥበቃ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ሀላፊው ከፓርኩ የሚወጣውን ፍሳሽ መልሶ በማጣራት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ገንብቶ ስራ ላይ እያዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከፍሳሽ የሚወጣውን ዝቃጭም በመለየት ለተለያዩ የግንባታ ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን እያመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሚኒስትር ዲኤታዋ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ የተመራው የጋዜጠኞች ቡድን በሀዋሳ የተለያዩ የልማት ስራዎችንና በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያደረገውን ጉብኝት በዛሬው ዕለት አጠናቋል።

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም