በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚያግዝ የክህሎት ካውንስል ወደ ሥራ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚያግዝ የክህሎት ካውንስል ወደ ሥራ ገባ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- በግብርና ምርቶች መቀነባበር ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚያግዝ የመጀመሪያው የዘርፍ ክህሎት ካውንስል በይፋ ሥራ መጀመሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
የዘርፍ ክህሎት ካውንስሉ 17 በሚሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባለሆኑ ተቋማቶች የተመሰረተ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 13 የግል ድርጅቶች አራቱ ደግሞ የመንግሥት ተቋማት መሆናቸው ተመላክቷል።
ካውንስሉ በዋናነት በግብርና ምርት መቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ ምን አይነት ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል? ብዛታቸውስና ለሥራው ምን አይነት ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል የሚሉ ነገሮች የመለየት ሥራን እንደሚሰራ ተገልጿል።
ይህንን የመለየት ሥራ ከተሰራ በኋላ ለግብርና ምርት መቀነባበሪያ ዘርፍ ምን አይነት ሥርዓተ-ትምህርት መዘጋጀት አለበት የሚለውን የሚያመላክት መሆኑን ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ካውንስሉ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ሥልጠና በተለያዩ ድርጅቶች ብሎም ኢንዱስትሪዎች ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ያስተባብራል ተብሏል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ መንግሥት በክህሎት፣ እውቀትና በሙያ የዳበረ ብቁ ዜጋን ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም በክህሎት የዳበሩ ዜጎችን ከማፍራት ረገድ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው በሚፈለገው ልክ ወደ ሥራ ከማስገባት አንጻርም ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
እነኚህን ውስንነቶች ለመቅረፍም መንግሥት ከሚሰራቸው ተግባራት ባሻገር የግሉ ዘርፍና የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ማፍራት የሚያስችለው የመጀመሪያው የዘርፍ ክህሎት ካውንስል ወደ ሥራ መግባቱም ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት ሞገስ፤ ካውንስሉ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ በተሰማሩ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና አጋር አካላትን በማስተባበር መመሥረቱን ተናግረዋል።
ካውንስሉ በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ከሰው ኃይል ልማት አንጻር የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።
በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በአለም አቀፍ ሥራ ድርጅት የፕሮ-አግሮ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማናጀር አንቶኒ አጀንታ በበኩላቸው ድርጅቱ ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ ላይ የምታከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።
በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ወደ ሥራ የገባው ካውንስል ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማሟላት ብሎም የዘርፉ ተዋናዮችን ቅንጅት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ለካውንስል ውጤታማ ሥራዎች ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።