ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠው ብድር ጨመረ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠው ብድር  መጨመሩ  ተመለከተ።

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ልማት ፖሊሲ ማዕከል ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው የቻይና አበዳሪዎች ባለፈው ዓመት ለአፍሪካ 4 ነጥብ 61 ቢሊዮን ዶላር ብድር ያጸደቁ ሲሆን፤ ይህም እ.አ.አ ከ2016 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳይቷል።  

አፍሪካ እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2018 ድረስ ከቻይና በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ማግኘቷን ጠቅሶ፤ የፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በ2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ብድሩ በፍጥነት ማሽቆልቆሉን ጥናቱ አመላክቷል።

ቻይና ከፍተኛ ዕዳ ካለባቸው ኢኮኖሚዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎችን ለመግታት ፍላጎት እንዳላትም ነው በጥናቱ የተመለከተው። 

የቻይና ብድር ለአፍሪካ ዳታቤዝ ፕሮጀክትን የሚያስተዳድረው የዩኒቨርሲቲው ማዕከል "ቤጂንግ የተሻለ ዘላቂ የሆነ የብድር ሚዛን ደረጃን የምትፈልግና  አዲስ ስትራቴጂን የምትሞክር ይመስላል ይላል ጥናቱ።

ይከው አዲስ መረጃ ቤጂንግ በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደውን የቻይና-አፍሪካ የትብብር መድረክ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በሚቀጥለው ሳምንት ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ እያለች የወጣ መሆኑን አንስቷል። 

ባለፈው ዓመት ስምንት የአፍሪካ ሀገራትና ሁለት የአፍሪካ የሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶችን ያካተተ 13 የብድር ስምምነቶች እንደነበሩ ጥናቱ ገልጿል።

ከቻይና ልማት ባንክ ባለፈው ዓመት ከተሰጡ ከፍተኛ ብድሮች መካከል ለናይጄሪያ ለካዱና-ካኖ የባቡር መስመር እና የግብፅ ማዕከላዊ ባንክ ለፈሳሽ መገልገያ መሳሪያ የሚውል የወሰደው አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር እንደሚጠቀሱ ዘገባው አመላክቷል።

ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የሁለትዮሽ አበዳሪ መሆኗንም አንስቷል።

አገሪቱ እ.አ.አ. ከ2000 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ለአፍሪካ 182 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ብድር መስጠቷን ጥናቱ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ከተሰጠው ብድር ውስጥ አብዛኛው ለኢነርጂ፣ ለትራንስፖርትና አይሲቲ ዘርፎች መሆኑን አመልክቷል።

ቻይና የምትሰጠው ብድር የቀነሰው በራሷ የውስጥ ችግሮች ግፊት እና በአፍሪካ ኢኮኖሚዎች መካከል እየጨመረ የመጣው የዕዳ ጫና መሆኑን ጥናቱ ማመልከቱን ዘገባው ገልጾ፤ ዛምቢያ፣ ጋና እና ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ የተራዘመ የዕዳ ማሻሻያ ለውጦች ውስጥ ገብተዋል ብሏል።

ባለፈው ዓመት ከተሰጡት ብድሮች ውስጥ 2 ነጥብ 59 ቢሊዮን ዶላር ለክልል እና ለሀገር አቀፍ አበዳሪዎች የተሰጠ ሲሆን፤ ይህም የቤጂንግ አዲሱን ስትራቴጂ የሚያጎላ መሆኑን ጥናቱ ጠቅሷል። 

"የቻይና አበዳሪዎች ለአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡት ትኩረት ለአፍሪካ ሀገራት የዕዳ ተግዳሮቶች መጋለጥን የሚያስወግድ የአደጋ መከላከል ስትራቴጂን ይወክላል" ብሏል።

እ.ኤ.አ. በ2023 ከተሰጠው ብደር አንድ አሥረኛው ያህሉ ለሦስት የፀሐይ እና የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መሆኑን ጥናቱ ማመላከቱን እና ቻይና ከድንጋይ ከሰል ኃይል ማመንጫዎች ይልቅ ታዳሽ ኃይልን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ያሳያል ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም