ቀጥታ፡

እርስ በርስ ያለው የመደጋገፍ እሴት አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት ሥራ የሚያጎለብት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- እርስ በርስ ያለው የመደጋገፍ እሴት አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት ሥራ የሚያጎለብት መሆኑን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አካባቢዎች በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚመለከታቸው አካላት ለተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መመሪያ መሰጠቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

ማኅበረሰቡም የተጎዱ ወገኖችን በሚቻለው ሁሉ እንዲደግፍም ጥሪ ማቅረባቸውም እንዲሁ።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ፓስተር ላኮ በዳሶ ተረክበዋል።

አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ማንንም ተጨማሪ አካል ሳንጠይቅ ሰፊ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል የሚያሳይ ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኃይማኖት ተቋማት በተደራጀ መንገድ የሚያደርጉት ድጋፍ የበለጠ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚከናወነውን ሥራ ረዥም ርቀት መውሰድ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ፓስተር ላኮ በዳሶ በበኩላቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ተከትሎ ድጋፉ መደረጉን ገልፀዋል።

በዚህም ለአጥቢያዎች ጥሪ መደረጉንና ለዚህ ፈጣን ድጋፍ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዛሬው ዕለት ይህ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

ድጋፉ በቀጣይም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ የቤተክርስቲያኑ የልማት ኮሚሽንም በቦታው ላይ አስፈላጊውን ቁሳቁስ እንዲያቀርብ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም