ቀጥታ፡

የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያና ቻይና የባህል ትስስራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያና ቻይና የሕዝብ ለሕዝብና የባህል ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑ ተመላከተ።  

በአዲስ አበባ የቻይናንን የሊያንግዙ ሥልጣኔ የሚያሳይ አውደ-ርዕይ ተካሂዷል።


 

በአውደ-ርዕዩ የቻይናን የሊያንግዙ ሥልጣኔ የሚያሳዩ የተለያዩ ታሪካዊ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ጥንታዊ ጽሑፎችና የፎቶ ምስሎች ቀርበዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው ስለሺ ግርማ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያና ቻይና ቀደምት የታሪክ፣ የባህልና የሥልጣኔ መነሻ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀደምት የሰው ዘር መገኛና የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አንስተው፤ ቻይናም ጥንታዊ የሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብና የባህል ትስስር እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከርና በልማት ዘርፍም ትብብሩን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሺን ኪንሚን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለዓለም የሥልጣኔ መነሻ ከመሆን ባለፈ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ታሪካዊ ያደርጋታል ነው ያሉት።


 

የቻይና ሥልጣኔ ከበርካታ ዓመታት በፊት ወንዝን ተከትሎ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህን ሥልጣኔ ከትውልድ ትውልድ አስጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና የብዝኃ ባህሎች ባለቤት እንደመሆናቸው ይህን ታሪክ አስጠብቀው ለትውልድ  ለማስተላለፍ መሥራት እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።

ቻይና ከአፍሪካ ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ባህላዊና ታሪካዊ ወዳጅነት በልማት መስኮች የበለጠ ለማጎልበት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሶናዝ፤ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በርከት ያሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን አንስተዋል።


 

ቻይናም በተመሳሳይ በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን በድርጅቱ በማስመዝገብ ታሪኳን ለዓለም እያስተዋወቀች ትገኛለች ብለዋል።

አገራት ያላቸውን ታሪክና ባህላዊ እሴት ሌሎች እንዲያውቁት ማድረጋቸው እርስ በርስ ለመተዋወቅ ከማስቻሉ ባለፈ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የባህል ልዩነትን ማክበር የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህል ልዩነቶች ውበት እንደመሆናቸው ጠብቆ ማቆየት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም