ቀጥታ፡

ባለፈው በጀት አመት ደህንነታቸው የተረጋገጠ መድሃኒቶች እና የምግብ አይነቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የተሻለ ስራ ተሰርቷል -ሄራን ገርባ

ድሬዳዋ ፤ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፈው በጀት አመት ደህንነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች እና የምግብ አይነቶች ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና እና ድህንነት ለመጠበቅ አበረታች ጥረት መደረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ገለፁ።

የዘርፉ አመታዊ የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የዘንድሮ አቅጣጫዎችን የሚገመግም ጉባኤ በድሬዳዋ ተካሄዷል።


 

ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሪት ሄራን ገርባ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው በጀት አመት በምግብ ደህንነት ቁጥጥር፣ ህገ ወጥ የመድሃኒት ንግድ በመከላከል፣ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀልን በመከላከል ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በበጀት አመቱ የምግብ ናሙናዎችን ጥራት በመመርመር ለ121 አዳዲስ የምግብ አምራቾች እና ለ953 የምግብ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች የብቃት ማረጋገጫ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለምግብና የምግብ ግብአቶች ተገቢውን ፍተሻ በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ፍቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው ምግብን ከበአድ ነገር ጋር የመቀላቀል ተግባራትን ለመከላከልም በምግብ ገበያ ማዕከላትና ችርቻሮ ድርጅቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል።

በተካሄደው የቁጥጥርና ምርመራ ስራ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ 542 ቶን የተለያዩ የምግብ አይነቶችን በማስወገድ 383 ተቋማት እንዲታገዱ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ  ዳይሬክተሯ ሄራን ገለፃ ከምግብ ምርቶች በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡ  የመድኃኒቶች ደህንነት፣ ጥራት እና ፈወሻነት በመከታተል እና በመቆጣጠር የተሰሩት ተግባራት ውጤታማ ናቸው።

ከነዚህ በተጨማሪ በህክምና መገልገያ መሣሪያዎች፣ በውበት መጠበቂያ ምርቶች፣ በትንባሆ እና በአልኮል ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል መደረጉን አመላክተዋል።

በተለይ የቁጥጥር እና ክትትሉን ስራ ዲጂታላይዝ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች መስጠት መጀመሩ አንዱ የለውጥ ምዕራፍ መሆኑን አውስተዋል።

የባለስልጣኑ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ቦጋለ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት አመት ከባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት በምስራቅ የአገራችን ክፍል በተከናወኑ በቁጥጥር እና ክትትል ስራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘቱን ተናግረዋል።


 

በተለይ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ መድኃኒቶች እና ምግቦች ላይ በተካሄደ ምርምራ ለህብረተሰቡ ጤና ችግር የሚፈጥሩ ግምታቸው ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚሆኑ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች እንዲወገዱ መደረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በድንበር ላይ በተሰሩ ስራዎች ከ2 ሚለየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ህገ ወጥ መድኃኒቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንስተዋል።

በጉባኤው ላይ የሁሉም ክልሎች፣የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም