ቀጥታ፡

በትምህርት ሴክተሩ ያሉ ባለድርሻ አካላት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- በትምህርት ሴክተሩ ያሉ ባለድርሻ አካላት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።

33ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ"ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም!" በሚል መሪ ሃሳብ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት  (ኮሜርስ)  መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው ላይ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የክልል የትምህርት ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገው የማሻሻያ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ይህም ማሻሻያ ስኬታማ ለማድረግ ለትምህርት ዘርፉ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ለዘርፉ ስኬት በአራት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልፀው፤ ጥራት፣ ፍትሃዊነት፣ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ  ማፍራትና ቅንጅታዊ አሠራር ማጎልበት እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህም በትምህርት ሴክተሩ ያሉ ባለድርሻ አካላት የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ ስኬታማ እንዲሆን በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን በማጤን የትምህርት ጥራትን፣ ፍትሃዊነትን እና ተደራሽነትን በማጎልበት በኩል ጉልህ እመርታ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል ። 

በ2017 የትምህርት ዘመን  የቅድመ አንደኛ ትምህርት የወደፊት የስኬት ዘሮች የሚዘሩበት መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።

የቅድመ አንደኛ ትምህርት ህጻናት ትምህርት የሚጀምሩበት ብቻ አይደለም፤ የአጠቃላይ የትምህርት ስርዓታችንን ጥራት የምንገነባበት መሰረት ነው ብለዋል።

በህጻናት ተማሪዎቻችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ በማተኮር የማስላት እና የቋንቋ ችሎታቸውን በፈጠራ እና በጨዋታ ላይ በተመሰረቱ አቀራረቦች በማጎልበት ለእድሜ ልክ ስኬት ማዘጋጀት ከኛ የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

 በጉባኤው  የሀገራዊ የትምህርት ስርዓታችንን ለማስጠበቅ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

ዛሬና ነገ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የ2016 ዓ.ም ትምህርት ዘርፍ አፈጻጸም፣ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችና የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም ላይ ያተኮረ  ውይይት ይካሄዳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም