ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካሳ ከፈለ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ገለጸ።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 37ኛውን ዓመታዊ ጉባዔና የድርጅቱ የ2016 በጀት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድን በተመለከተ ውይይት እያካሄደ ነው።


 

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ለቀረቡ ለሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለደረሰ አደጋ እንዲሁም በሕጋዊ ኃላፊነት ምክንያት ለድርጅቱ በቀረቡ ጥያቄዎች 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የካሳ ክፍያ ተፈጽሟል።

ይህም መጠን ከዕቅድ አንጻር የ18 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽና ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተከፈለው ጋር ሲነጻጸር 13 ነጥብ 8 ቅናሽ ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ የጉዳት ካሳ ምጣኔ 52 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዕቅዱም ሆነ ከኢንዱስትሪው የጉዳት ካሳ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 178 ሺህ ውሎች ሽያጭና የእድሳት አገልግሎት መከናወኑን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን የአረቦን ገቢ የተመዘገበ ሲሆን፤ በዚህም ድርጅቱ የዕቅዱን 92 ነጥብ 4 በመቶ ማሳካት ችሏል ብለዋል።

የድርጅቱ የአረቦን ገቢ ከኢንዱስትሪው ጠቅላላ አረቦን 30 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።

በጠቅላላው ድርጅቱ በ2016 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ከታክስ በፊት አስመዝግቧል ብለዋል።

የተገኘው ውጤት ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በ7 ነጥብ 5 በመቶና ካለፈው በጀት ዓመት ደግሞ በ15 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዛሬ ያስጀመረው 37ኛው ዓመታዊ ጉባዔ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም