ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለውሹ ማርሻል አርት ስፖርት አሰልጣኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ሲኒየር ግራንድ ማስተር’ ዳን ሊሰጥ ነው   

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ለውሹ ማርሻል አርት ስፖርት አሰልጣኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ሲኒየር ግራንድ ማስተር’ ዳን እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ከቻይናው ውሹ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተወጣጡ 200 የውሹ አሰልጣኞች በአዲስ አበባ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ስልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት ዓለም አቀፉ የውሹ ማርሻል አርት ስፖርት ማስተር ፊንግ ናቸው።

ማስተር ፊንግ የዳን ስልጠናና ምዘናዎችን ካጠናቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሰልጣኞች መጨረሻ ደረጃ ‘ሲኒየር ግራንድ ማስተር’ ዳን እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡


 

የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማስተር አቡበከር አህመድ የውሹ ማርሻል አርት ስፖርት የፈጠራ ክህሎትን ለማጎልበት፣አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት ለመጠበቅና ጠንካራ ትውልድ ለማፍራት የሚያግዝ የስፖርት አይነት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም በስፖርቱ ተወዳዳሪ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር የውሹ ማርሻል አርት ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታ እንደሚከናወን ገልጸው መንግስት የግንባታ ቦታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

የአሰልጣኞች ስልጠናው እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም