ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ለተለያዩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በልማት ፈንዱ ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶናል ብራውን ከተመራ የከፍተኛ አመራሮች ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በአሁኑ ወቅት በትግበራ ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችና በቆላማ አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል አላማ ያደረገው ፕሮጀክት (LLRP) የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝና ዘርፉ ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶናል ብራውን የልማት ፈንዱና ኢትዮጵያ ያላቸው አጋርነት በአፍሪካ ትልቁና ውጤታማ ትብብር እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ወደ ስራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎችን አድንቀዋል።


 

የልማት ፈንዱ በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኙና በቀጣይ ለሚገነቡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማሳደግ እንደሚሻ ገልጸዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እየተገበራቸው ለሚገኘው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማትና ዘላቂ ምርታማነት ፕሮግራም (CRISP) እና የአነስተኛ ልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ከሚደረግላቸው መርሐ ግብሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

ሁለቱ ተቋማት የግሉ ዘርፍ በፕሮጀክቶቹ ላይ መዋዕለ ነዋዩን እንዲያፈስ ማበረታቻዎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ አሰራሮች እንዲመጡና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም