ቀጥታ፡

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የነፃ ምርመራ አገልግሎት ይሰጣል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):- ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መርኃ ግብሩ ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን  2016 ዓ.ም የሚቆይ የነፃ ምርመራ አገልግሎት ሊሰጥ ነው። 

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ኃይሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ማዕከሉ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ይህንንም ተከትሎ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የነፃ ምርመራ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ነጻ የህክምና አገልግሎቱ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ፣ የራጅ፣ ኢንዶስኮፒና በማዕከሉ የሚሰጡ ሌሎች የምርመራ አገልግሎቶች የሚያካትት መሆኑን ጠቁመዋል። 

ከመንግሥት የሕክምና ተቋማት በሐኪም ምርመራ ታዞላቸው በአቅም ውስንነት ምርመራው ለማድረግ ያልቻሉ ወገኖቻችን የነጻ ሕክምናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ተወካይ የሆኑት ዶክተር አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው የጤና ተቋሙ በየጊዜው  የሚሰጠው ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚበረታታ ነው ብለዋል። 

ሌሎች የሕክምና ተቋማትም አርአያነቱ ሊከተሉት እንደሚገባ አንስተዋል።

ማዕከሉ ባለፉት 14 ዓመታት መሰል ነጻ የሕክምና ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ከ54 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተጠቅሷል። 


 

ጎን ለጎንም ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የስፖርት ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ለማቋቋም የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራና የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ኃይሉ ፈርመውታል። 

በማዕከሉ የሚደራጀው የስፖርት ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ለስፖርቱ ማኅበረሰብና ከዚያም ባሻገር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም