የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ነገ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ነገ ይጀምራል
ሆሳዕና ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራውን ነገ እንደሚጀምር አስታወቀ ፡፡
ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ዛሬ በሆሳዕና ከተማ በሰጠው መግለጫ በክልሉ ከነገ ጀምሮ አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩን እንደሚጀምር አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት የሀገሪቱ ዜጎች ችግሮቻቸውን በምክክር እንዲፈቱ ለማስቻል የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የተለያዩ አስፈላጊ ስራዎችን በማጠናቀቅ አሁን ላይ አጀንዳ ወደማሰባሰብ ሂደት ላይ መሸጋገሩን ጠቅሰው በሌሎች ክልሎችም አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በዚህ ሳምንት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ተመሳሳይ ተግባሩን እንደሚያከናውን አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ከነገ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት አጀንዳ የማሰባሰብ ስራን ለማከናወን የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
በሂደቱም በክልሉ ከሚገኙ ሰባት ዞኖችና ሶስት ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በዚህም ከወከሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰቧቸውን አጀንዳዎች በማቅረብ የማጠቃለያ ውይይት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
" እንደሀገር ዘመናት የተሻገሩና ያደሩ ችግሮቻችንን በመመካከር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣትና ማከም ይጠበቅብናል" ያሉት ኮሚሽነሩ "ይህም የምክክሩን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ አጋዥ ነው" ሲሉ አክለዋል ።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች አካታችነት፣ ግልፀኝነትን፣ አሳታፊነትንና ተዓማኒነትን መሰረት በማድረግ ለምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ሀገሪቱን ከተለያዩ ችግሮች በማላቀቅ ብሩህ ተስፋዋን ለማስቀጠል ከፍተኛ ውጤት እንደሚኖረው የታመነበት ታሪካዊ ሂደት ከግብ እንዲደርስ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።