ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በዲጂታል ዘርፍ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያና አዘርባጃን በዲጂታል ዘርፍ በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች ከአዘርባጃን መንግስት ልዑካን ቡድን ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማዘመንና በዲጂታል ስራዎች በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ አዘርባጃን በዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ያላትን ልምድ መቅሰም እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ዜጎች በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣንና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆን ለማድረግ የኢሰርቪስ አገልግሎቶችን በመዘርጋት ላይ ይገኛል ብለዋል።

አገልግሎቱን ለማስፋፋትና በሁሉም ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ ከአዘርባጃን መንግስት ጋር አብረን መስራት እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የአዘርባጃን መንግስት የሕዝብ አገልግሎትና ማህበራዊ ፈጠራዎች ኤጀንሲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ማህመድሊ ክሁዳቨርዲዬቭ ዜጎች በቀላሉ ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፤ ለዚህም የኢ ሰርቪስ አገልግሎት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።


 

የአዘርባጃን መንግስት በዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልግ መግለጻቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራን ለማፋጠንና ተሞክሮዎች መለዋወጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር መደረጉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም