ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት አላት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ።

የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚፃረሩ አካላትን ከማስተናገድ ሊቆጠብ እንደሚገባም አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገልጸዋል።


 

በመግለጫቸውም፤የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት መሠረት ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልፀዋል።

በዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር በባህልና መሰል ታሪካዊ ወዳጅነትን በማስቀጠል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራ አገር መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲ ወዳጅነት የመንግሥታት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በባህልና በሕዝብ ለሕዝብ ጭምር የተሳሰረ መሆኑንም ገልፀዋል።

እንዲያም ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ከጎረቤቶቻችን መካከል ከሶማሊያ ጋር ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረትን እየሳበ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በኢትዮ-ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ወቅታዊ አለመግባባት በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት በተርኪዬና በኬንያ የተደረገው ውይይት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደነበር ገልፀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የሚነሱ ችግሮችን በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ መፍትሔ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አጽንዖት ሰጥተዋል።

ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሆኖ እያለም አንዳንድ የሶማሊያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአገራቱ መካከል ልዩነትን የሚያሰፋ ድርጊት ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ እንደ አገር እንድትቋቋም ያልተቆጠበ የደም፣ ጉልበትና የላብ ድጋፍ መስጠቷን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የከፈለችውን ዋጋ ማኮሰስ ያማልም ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የከፈለችውን ውድ ዋጋ የሚያንኳስሱና የሚያጣጥሉ አንዳንድ የሶማሊያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ተገቢነት የሌለው መሆኑን አስምረውበታል።

በቀጣይም የአገራቱን የጋራ እጣ ፈንታ፣ ወዳጅነትና ትብብር ለማጠናከር መሥራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የከፈልነውን ውድ መስዋትነት ማጣጣል ተገቢ አይደለም፤ በጋራ ሲደረግ የነበረውን የፀረ-ሽብር ትግል አጠናክረን እንድንቀጥል መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሶማሊያ መንግሥትም ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ፍላጎት የሌላቸው አካላትን በአንክሮ ማየት ይገባዋል ብለዋል።

የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ አካላትን ከማስተናገድ መቆጠብ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም