ህዝቡን በማስተባበር ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራን ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡን በማስተባበር ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራን ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ
ሶዶ ፤ ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ):- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብን አስተባብረን በመስራት የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
የክልሉን አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ህዝብን በማስተባበር ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ ነው።
በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ ሰላምን ለማጽናት ነባርና ቱባ የሆኑትን ማህበራዊ የሰላም ግንባታ ዕሴቶችና የሕዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ውጤት መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ክልሉ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና በመሰል ዘርፎች ያሉትን ጸጋዎች ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል የዕድገት ዘርፎች ተለይተውና ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
በተለይም ክልሉ ካሉት አቅሞች የግብርናውን ዘርፍ ከአምራች ኢንዱስትሪ ጋር አስተሳስሮ እሴት ጨምሮ በማምረት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘት እንደተቻለ አንስተዋል።
በዚህም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተሻለ እንቅስቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።
ክልሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡትን ጨምሮ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን አስታውሰው፣ መስህቦቹን በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ገቢ ለማግኘት በሁሉም አካባቢዎች በተቀናጀ መንገድ በተደረገው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
ክልሉ የታደላቸውን ጸጋዎች አውጥተንና አሟጦ በመጠቀም የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የሚከናወነው ሥራን ከግብ ለማድረስ የሰው ኃይል ለማብቃት የተሰጠው ትኩረትም ትልቅ ነው ብለዋል።
የምንሰራቸው ተግባራት በህዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጡ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ ሕዝብ በየአካባቢው ያሉትን ጸጋዎች በአግባቡ ለይቶ በትጋት በመስራት ልማትን ለማረጋገጥ በተቀናጀ መንገድ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ12 ዞኖች የተዋቀረና ስድስት ማዕከላት ያሉት ሲሆን፣ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ሰሞኑን ማክበሩ ይታወሳል።