የአየር ትንበያ መረጃን በአግባቡ ተደራሽ በማድረግና በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ መረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ትንበያ መረጃን በአግባቡ ተደራሽ በማድረግና በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ መረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ
አዳማ፤ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ)፡-የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃን በአግባቡ ተደራሽ በማድረግና በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ መረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ።
የ2016 ዓ.ም የክረምት አየር ጠባይ የአየር ሁኔታ ግምገማና የቀጣይ ዓመት የበጋ ወራት የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያና ይፋ ማድረጊያ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ እንደገለጹት፤ የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ ላይ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም መረጃው በአግባቡ መጠቀም ላይ ክፍተት አለ።
በዚህም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተለይ በወንዞች ዳር የሚኖሩ ዜጎች ተገቢው የአየር ትንበያ መረጃ በአግባቡ ባለማድረሱ አሁንም በጎርፍና በመሬት መንሸራተት እየተጎዱ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ ክረምትም የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች፣ ግድቦችና ወንዞች ሞልተው ዜጎችን ለችግር ሊዳርጉ የሚችሉ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የአየር ትንበያ መረጃውን በአግባቡ በመጠቀምና በቅድመ ጥንቃቄ ስራ ላይ በትኩረት በመስረት ችግሮቹን መቀነስ የሚያስችል በመሆኑ የዘርፍ አመራር አባለት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
''የጎርፍ ውሃን ወደ ዕድል መቀየር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት አለብን'' ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ(ዶ/ር) ''ለዚህም በአጭርና በረዥም ጊዜ ዕቅድ ለማውጣት ባለድርሻ አካላት ተናበን መስራት ይጠበቅብናል'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው የዘንድሮው የክረምት የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሀገሪቷ መኖሩን ያመላከተ ነበር ብለዋል።
በዚህም ለግብርና ልማት በተለይ ለሰብል ልማት ምርትና ምርታማነት አመቺ መሆኑን አመልክተው ግብርና፣ ለጤና፣ ትምህርትና ትራንስፖርት ለማሳለጥ ተገቢውን የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃን በመስጠት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የመጪው የበጋ ወቅት የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ቦረና፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵ ክልሎች መደበኛ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን ደቡባዊው የሶማሌ ክልል ዞኖች ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ላይ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።