ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ከግብር በፊት ትርፍ አገኘ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ከግብር በፊት ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ። 

የኢትዮጵያ  መድን  ድርጅት  37ኛውን  ዓመታዊ ጉባዔ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የድርጅቱ ኃላፊዎችና  የድርጅቱ የሥራ አመራሮች ጋር እያካሄደ ነው።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ እንደገለፁት፤ በ2016 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ከታክስ በፊት አስመዝግቧል ብለዋል። 


 

የተገኘው ውጤት ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በ7 ነጥብ 5 በመቶ እና ካለፈው በጀት ዓመት ውጤት ደግሞ በ15 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል። 

የአረቦን ገቢን በተመለከተ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የአረቦን ገቢ የተመዘገበ ሲሆን፤ በዚህም ድርጅቱ የዕቅዱን 92 ነጥብ 4 በመቶ ማሳካት ችሏል ብለዋል።  

ድርጅቱ ያስመዘገበው አረቦን ከኢንዱስትሪው ጠቅላላ አረቦን ያለው ድርሻ 30 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የ178 ሺህ 970 ውሎች ሽያጭና እድሳት ተከናውኗል። 

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት 10 ነጥብ 9 በመቶ አፈጻጸም ከፍ ያለ ሲሆን፤ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ቁጥር ማሳካት የተቻለው 96 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑ ነው የተገለፀው።  

ለተስተናገዱት ውሎች የተሰጠው የዋስትና ሽፋን መጠን ብር 6 ነጥብ 4 ትሪሊየን የደረሰ ሲሆን፤ ይህም መጠን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ43 ነጥብ 9 በመቶ እድገት አሳይቷል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም