በኦሮሚያ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 27 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 27 ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 24/2016(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜን 5 ድረስ እንደሚካሄድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ግርማ ባይሳ፤ የ2017 የትምህርት ዘመንን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በ2017 የትምህርት ዘመን በኦሮሚያ ክልል ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጆች ድረስ በ37 ሺህ 959 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት ይከናወናል ብለዋል።
በዚህም የኮሌጆችን ሳይጨምር ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ12 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በክረምቱ ወራት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ 1 ሺህ 939 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ከ6 ሺህ በላይ ለሆኑ የመማሪያ ክፍሎችም ጥገና መከናወኑንም ተናግረዋል።
በክረምቱ ወራት 1 ሺህ 114 ቤተ-መጽሐፍት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ የ2017 ትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜን 5 ድረስ የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመማር ማስተማር ሂደትም መስከረም 7 እንደሚጀመር አክለው ገልፀዋል።
ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙም ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።