በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አራት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አራት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2016 (ኢዜአ)፦በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የአራተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አራት የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የሜዳሊያ ሰንጠረዥ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ25 ላይ የሴቶች 10000 ሜትር እርምጃ የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።አትሌት ሕይወት አምባውና አትሌት ብርሃን ሙሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ሕይወት በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 46 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ20 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች።
ሌላኛዋ አትሌት ብርሃን ሙሉ በተመሳሳይ በሃዋሳ በተካሄደው ውድድር 46 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገብ ችላለች።
ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ35 በሚካሄደው የወንዶች 800 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ጀነራል ብርሃኑ ይወዳደራል።
አትሌት ጀነራል በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 1 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
አትሌት አስቴር አሬሬ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ50 ላይ በሚካሄደው የሴቶች 800 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ትሳተፋለች።
አትሌት አስቴር በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች 2 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ5 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች።
ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ላይ በሚደረገው የ3000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አትሌት አለሺኝ ባወቀና አትሌት ማርታ አለማየሁ ይወዳደራሉ።
አትሌት አለሺኝ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 8 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያ አትሌት ማርታ አለማየሁ በተመሳሳይ በሃዋሳ በተደረገው ውድድር 8 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ40 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች።
በፔሩ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅና በሁለት የብር በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት አንደኛ ደረጃን ይዛለች።
ደቡብ አፍሪካ በሁለት የወርቅ፣ 1 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
አውስትራሊያ በሁለት የወርቅና በሁለት የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
አሜሪካ፣ቻይና፣ ኬንያና ቼክ ሪፐብሊክ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
እስከ አሁን 26 አገራት ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።
ሻምፒዮናው ነገ ይጠናቀቃል።