ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የፀጥታ ተቋማት አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸውን የፀጥታ ተቋማት አስታወቀዋል።

“ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ዓድዋ መታሰቢያ የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ይካሔዳል።

ፎረሙ በሰላም እንዲካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸውንም የፀጥታ ተቋማት በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ባደረጉት የጋራ ውይይት አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ እንዳሉት የፀጥታ ተቋማቱ በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ ገብተዋል።


 

በፎረሙ ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት ወደ መዲናዋ የሚመጡ የአፍሪካ ሀገራት ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ በሀገራችን የሚገኙ የትላልቅ ከተማ ከንቲባዎች እና ሚኒስትሮች እንዲሁም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ደኅንነት ማረጋገጥ የፀጥታ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በከተማዋ የተካሄዱ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ፎረሙ በስኬት እንዲካሄድ ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅተው በመስራት እንደወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም መልዕክት መተላለፉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም