የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ መላው ዓለም በአርዓያነት ሊከተለው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ የተከሉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ መላው ዓለም በአርዓያነት ሊከተለው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገለጹ።

''የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ'' በሚል መሪ ቃል ለ6ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘውን የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዓላማ የደገፉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ መትከላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች ኢትዮጵያ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሥነ-ምህዳር በመፍጠርና የካርበን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ መላው ዓለም በአርዓያነት ሊከተለው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍንና ደኅንነት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና የምትጫወት ስትራቴጂክ ሀገር መሆኗን የመሰከሩት የኤምባሲዎቹ ተወካዮች፤ በመረጃ ልውውጥና በተለያዩ የአጋርነት መስኮች የሚደረጉ ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መጠቆማቸውንም መረጃው ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም