የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የሚዲያ ፎረም በቻይና ቼንግዱ ከተማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የሚዲያ ፎረም በቻይና ቼንግዱ ከተማ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦ትኩረቱን የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ላይ ያደረገው የ2024 የሚዲያ ፎረም በቻይና ሲሹዋን ግዛት በምትገኘው ቼንግዱ ከተማ ተካሄዷል።
ፎረሙ የተካሄደው “የሚዲያ ትብብር እድገት ለጋራ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው።
በፎረሙ ላይ በ76 አገራት ከሚገኙ 191 ተቋማት የተወጣጡ ከ200 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ ኤዲተሮችና ጋዜጠኞች መሳተፋቸውን የቻይናው ፒፕልስ ዴይሊ ጋዜጣ በድረ ገጹ አስፍሯል።
ከተሳታፊ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይገኝበታል።
የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ አባልና የማዕከላዊ ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙንት የስራ ክፍል ኃላፊ ሊ ሹሌ በፎረሙ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።
በፎረሙ ላይ የተሳተፉ ልዑካን እ.አ.አ በ2013 የተጀመረው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በፍጥነት አድጎ ተጨባጭና ትልቅ ውጤቶች ማምጣቱን ገልጸዋል።
በኢኒሼቲቩ አማካኝነት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የተሳሰረች ዓለም በመፍጠር ጥረት ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ ይህም የተናጥልና የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ምቹ መደላልድል መፍጠሩን አመልክተዋል።
መገናኛ ብዙሃን ኢኒሼቲቩ የፈጠረውን የጋራ ትብብርና ያስገኛቸውን የልማት ስኬቶች ከማጉላት አንጻር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፎረሙ ተሳታፊዎች መገናኛ ብዙሃን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት በማድረግ የፈጠረውን ትብብርና ለዓለም ያበረከተውን አስተዋጽኦ በዘገባዎቻቸው ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያመጣቸውን ፈተናዎች በማመላከት ቴክኖሎጂው ትስስርን በማጎልበትና የዲጂታልና የክህሎት አቅሞችን በማሳደግ ያለውን ሚና ይበልጥ በማጉላት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃንን ትብብርና የባህል የልምድ ልውውጥን ማዳበር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ በስፋት የተነሳ ሀሳብ ነው።
የአገራትን ጊዜ የማይሽራቸውን ታሪኮችና ባህሎች ከዘመናዊ እሴቶች ጋር አጣጥሞ በማስኬድ የጋራ መግባባትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ በመጠቆም።
በፎረሙ ላይ የቤልት ኤንድ ሮድ የሚዲያ ትብብር ቼንግዱ ኢኒሼቲቭ ይፋ ሆኗል። በተጨማሪም የፎረሙ አካል የሆነ የቤልትና ሮድ ኢኒሼቲቭ ኒውስ ኔትወርክ ምክር ቤት ሶስተኛ ስብስባ ተከናውኗል።
የሚዲያ ፎረሙን ያዘጋጁት ፒፕልስ ዴይሊ ጋዜጣ፣ የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ የሲሹዋን ግዛት ኮሚቴና የሲሹዋን ግዛት መንግስት በጋራ በመተባበር መሆኑ ተጠቁሟል።
እ.አ.አ በ2013 የተጀመረው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ከ4 እስከ 8 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የተቀረጸው አውሮፓንና እስያን ማዕከል አድርጎ በአፍሪካና ሌሎች አህጉራት የሚገኙ አገራትን በየብስና በውሃ ትራንስፖርት ጨምሮ በዘርፈ ብዙ መሰረተ ልማቶች ማስተሳሰርን አላማ በማድረግ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።ዋነኛ ግቡም በአገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ ነው።
የትብብር ማዕቀፉን ሰነድ በመቀበል እስከ አሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ150 በላይ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ፊርማቸውን አኑረዋል።