ቀጥታ፡

በበቆሎ ምርት ላይ የተደረጉ ምርምሮች ለምርቱ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ በበቆሎ ምርት ላይ የተደረጉ ምርምሮችና አዳዲስ አሠራሮች ለምርቱ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የበቆሎ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዓላማ አድርጎ በየአሥር ዓመቱ የሚካሄደው አራተኛው ሀገር አቀፍ አውደ-ጥናት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡


 

በአውደ-ጥናቱ ላይም በቆሎ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ከሆኑ ሰብሎች መካከል አንዱ መሆኑ ተነስቷል።

እያደገ ለመጣው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚሆኑ ዋነኛ የሰብል ዓይነቶች መካከልም አንዱ መሆኑ ተመላክቷል።

በለውጡ ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በቆሎን በኩታገጠም በማምረት ምርታማነቱ ከፍ እንዲል እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር)፤ ባለፉት ዓመታት በበቆሎ ምርት ላይ የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው አንስተዋል።

በበቆሎ ምርት ላይ ከ48 በላይ የምርምር ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ በቆሎን በኩታገጠም በማምረት ምርታማነት ጨምሯል ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የበቆሎ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ(ዶ/ር)፤ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው አውደ-ጥናት ባለፉት አሥር ዓመታት በበቆሎ ምርምር ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎች የሚዳሰሱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከምርምር ማዕከላት የወጡ ምርጥ ዘሮች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ፋይዳው ይዳሰሳል ብለዋል።

የበቆሎ ምርታማነትን ይበልጥ ከማሳደግ አንጻር ሊሰሩ በሚገባቸው ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያም ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በበቆሎ ምርምር ዘርፍ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የተዳቀለ የበቆሎ ዝርያ ያስተዋወቀች ሀገር መሆኗን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በዚህም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቁመው፤ የበቆሎ ምርታማነት በሄክታር ከ20 ኩንታል ወደ 46 ኩንታል ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ ከሚሰራባቸው 11 የሰብል ዓይነቶች መካከል በቆሎ አንዱ ነው ብለዋል፡፡

በቆሎ ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በበቆሎ ምርት ራሷን የቻለች ሀገር ናት ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ፤ ወደፊት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

በአውደ-ጥናቱ ላይ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ምርምር ባለሙያዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም