የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የላቀ እውቀትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች የተሳካ አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የላቀ እውቀትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች የተሳካ አገልግሎት እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የላቀ እውቀትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች የተሳካ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሴክዩሪቲና ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር ደበበ ግርማ፤ ባለሥልጣኑ የበረራ ደኅንነትን አስተማማኝ በማድረግ ረገድ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የበረራ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች በመከተል ጥብቅ የበረራ ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የአቪዬሽን ዘርፉ በእውቀትና ክህሎት የላቀ ብቃት በተላበሱ ባለሙያዎች ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በዚህ የአሠራር ሂደት ማናቸውም የበረራ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የአቪዬሽንን ሕግ የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው አንስተዋል።
ከአቪዬሽን አሠራር ጋር በተገናኘ ተገልጋዮች በአየር መንገዱ ሠራተኞች የሚተላለፉ ደንብና መመሪያዎችን አክብሮ መንቀሳቀስና ለጋራ ደኅንነት ተባባሪ መሆንም ይጠበቃል ብለዋል።
የበረራ ደኅንነትን አስተማማኝ በማድረግ ረገድ ባለሥልጣኑ ከዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
በባለሥልጣኑ የአየር ትራፊክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር ዮሐንስ አበራ፤ በዓለም ላይ አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት ከሚሰጡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎቱ የአፍሪካ ኩራትና የሀገር ምልክት በመሆን ዘመናትን የተሻገረ ግዙፍ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ይህንን ስምና ክብር አስጠብቆ፣ የአገልግሎቱን አድማስ አሳድጎ የማስቀጠል ሥራ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በርካታ ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።