ለሰራተኞች ነፃ የህክምና ምርመራ መደረጉ ያሉበትን የጤና ሁኔታ አውቀው ቀጣይ ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ይረዳል - ኢዜአ አማርኛ
ለሰራተኞች ነፃ የህክምና ምርመራ መደረጉ ያሉበትን የጤና ሁኔታ አውቀው ቀጣይ ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ይረዳል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ለሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ነፃ የህክምና ምርመራ መደረጉ የጤና ሁኔታቸውን አውቀው ቀጣይ ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ እንደሚረዳ ተገለፀ፡፡
የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል ለኢዜአ ሰራተኞች ነጻ የህክምና ምርመራ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ሆስፒታሉ የህክምና ምርመራ አገልግሎቱን በኢዜአ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት የሰጠ ሲሆን ምርመራውም የደም ግፊት፣የስኳርና ከአንገት በላይ ህመሞች መሆኑ ተገልጿል።
የሆስፒታሉ የስልጠናና ምርምር ኃላፊ ዱሬሳ እንዳለ እንደገጹት ለሰራተኞቹ የተሰጠው የምርመራ መርኃ ግብር ሆስፒታሉ በየዓመቱ ለተለያዩ አካላት የሚሰጠው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጌርጌሶኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ተመሳሳይ ነጻ የህክምና ምርመራ መስጠቱንና ክረምቱ አስከሚያልቅም በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ ታክሲ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በየቀኑ የስኳር፣የደም ግፊት፣የቲቢ፣የአይን፣የጆሮ ህመሞች ምርመራ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ሆስፒታሉ ከሚያከናውነው የምርመራና የምክር አገልግሎት ባሻገር የህመም ምልክት ለታየባቸው ሰዎች ቀጣይ የህክምና አገልግሎትና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ተቋማት ከህክምና ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለሰራተኞቻቸው ነጻ የምርመራ አገልግሎት የመስጠት ባህል ማደግ እንዳለበት ያስገነዘቡት ኃላፊው ኢዜአ ሰራተኞቹ በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ የጤና ሁኔታቸውን እንዲያውቁና የህክምና ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ስራ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የኢዜአ ባልደረባ ወይዘሮ ዘይነባ ዳውድ በነጻ የምርመራ አገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆን የጤና ሁኔታቸውን እንዳወቁ የገለፁ ሲሆን እንዲህ ያሉ በጎ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሌላው የኢዜአ ባልደረባ ሻምበል ጥላሁን እንደሚሉት ህመም ሲሰማ ብቻ ወደ ህክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ ቀድሞ የጤና ሁኔታን ማወቅና ከባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ማግኘት ሊለመድ የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል ጋር በትብብር ያደረገው ነጻ የህክምና ምርመራ በሌሎች ተቋማትም ሊለመድ እንደሚገባም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ በበኩላቸው ራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል እና ኢዜአ በትብብር ለተቋሙ ሰራተኞች ነጻ የህክምና ምርመራ አገልግሎት መስጠታቸው ሰራተኞች ያሉበትን የጤና ሁኔታ አውቀው ቀጣይ ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት።
ኢዜአ ሰራተኞቹ በጤናማነት ስራቸውን እንዲያከናውኑ ከህክምና ተቋማት ጋር በቅንጅት ከመስራት ባሻገር በተቋሙ ቅጥር ግቢ የስፖርት ጂምናዚየም ገንብቶ ለአገልግሎት እንዳበቃም አክለዋል።
እንዲህ ያሉ ልምዶች ሰራተኞች ጤናማ የስራ ውሎ እንዲያሳልፉ ከማገዛቸውም ባሻገር በስራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክቱ ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ እንዳሉት ተቋሙ ሰራተኞች በቂ የህክምና ክትትል እንዲያገኙ ከህክምና ተቋማት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።