ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞንን ዋንጫ በማንሳት በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞንን ዋንጫ በማንሳት በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን አረጋገጠ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞን ዋንጫን በማንሳት በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ መሳተፉን አረጋግጧል።
ንግድ ባንክ የፍጻሜው ጨዋታ የኬንያውን ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስን 1 ለ 0 በማሸነፍ ምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካን በመወከል የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የሚሳተፍ ይሆናል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በ78ኛው ደቂቃ በአስደናቂ ቅብብሎሽ የተገኘውን ኳስ አጥቂዋ ሴናፋ ዋቁማ ከመረብ ላይ በማሳረፍ ንግድ ባንክን አሸናፊ አድርጋለች።
ሁለቱ የፍጻሜ ተፋላሚ ክለቦች በማጣሪያው በምድብ አንድ ተገናኝተው ነበር።
በጨዋታው ሴናፍ ዋቁማ ባስቆጠረቻቸው ግቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ውድድሩን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ መሳተፉን አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞንን ወክሎ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።
አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ በማጣሪያው ላይ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቃለች።
በጨዋታው በርካታ ደጋፊዎች በስታዲየሙ በመገኘት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አበረታተዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሶስት የማጣሪያ ተሳትፎዎች በሁለቱ ፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ባስመዘገባቸው ውጤቶች ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ ሳይችል ቀርቶ ነበር።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ምክትል ፕሬዝዳንት ሱሌይማን ዋቤሪ፣ የምስራቅና መካከለኛው የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ፕሬዝዳንት ዋላስ ካርያ፣ የዩጋንዳና ብሩንዲ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች እንግዶች በፍጻሜው ጨዋታ ላይ ታድመዋል።
ከነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የማጣሪያው ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።